የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በሱናሚ አደጋ ወቅት ለጃፓን ሕዝብ ያሳዩት ጠንካራ አጋርነት የሚደነቅ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2004 (ዋኢማ) – የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ባለፈው ዓመት በጃፓን በደረሰው ርዕደ መሬትና የሱናሚ አደጋ ለጃፓን ሕዝብ ያሳዩትን ጠንካራ አጋርነት መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ገለጹ፡፡ የአደጋው አንደኛ ዓመት ዛሬ በመላው ዓለም ታስቦ ውሏል፡፡

አምባሳደር ሂሮዮኪ ኪሺኖ አደጋው የተከሰተበትን አንደኛ ዓመት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በታሰበበት ወቅት እንዳሉት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጃፓን ባጋጠማት አደጋ የተሰማቸውን ጥልቅ ኃዘን ከመግለጽ ባሻገር የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለጃፓናውያን ያላቸውን አጋርነት በተግባር አሳይተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሪቱ ያለውን አጋርነት ለማሳየት ከ5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን የኃይማኖት ተቋማትም በአደጋው ሰለባ ለሆነው የጃፓን ሕዝብ በጸሎት ድጋፍ ማድረጋቸው በጃፓን ሕዝብና መንግሥት ስም አምባሳደሩ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

” በዚህ አጋጣሚ በጃፓን ሕዝብና መንግሥት ስም ጃፓን በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ድጋፍ ላደረጉት ሁሉ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ የተደረገልን መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም፡፡”

ባለፈው ዓመት በዚህ ወር ምስራቃዊ ጃፓን በከፍተኛ የመሬት ነውጥና የሱናሚ አደጋ ሲመታ ቤትና ተሽከርካሪዎች እንዲሁም መርከቦች ልክ እንደ አሻንጉሊት በሱናሚው ማዕበል ሲወረወሩ ዓለምን ጉድ አሰኝቶ ነበር፡፡

በአደጋውም 16 ሺህ ያህል ሰዎች ሰለባ ሲሆኑ ከ3 ሺህ በላይ ደግሞ የት እንደደረሱ ዛሬ ድረስ አልታወቀም፡፡

በአደጋው በተመታው ምስራቃዊ የባህር ዳርቻ የአገሪቱ ክፍል የነበሩ ከተሞችም በአብዛኛው በአደጋው የወደሙ ሲሆን በርካታ ነዋሪዎቻቸውም ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡

ያም ሆኖ የጃፓን ሕዝብና መንግሥት እንዲሁም ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም ማኅበረሰብ ባደረጉት ርብርብ የመልሶ ማቋቋምና የመልሶ ግንባታ ሥራው በተፋጠነ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ አምባሳደር ኪሺኖ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም በአብዛኛው የአገሪቷ ክፍል የተረጋጋ ኑሮ መቀጠሉን ጠቁመው ቁልፍ የሆኑ የመሰረተ ልማት አውታሮችንም ቀድሞ ወደነበሩበት ገጽታ መመለስ እንደተቻለ አመልክተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በዚሁ ወቅት ባሰሙት ንግግር ባለፈው ዓመት በጃፓን በደረሰው አደጋ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በእጅጉ ማዘኑን ገልጸዋል፡፡

ጃፓን በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ሚና የምትጫወት አገር እንደመሆኗ መጠን የአገሪቱ መረጋጋትና ብልጽግና እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በተለይ ጃፓን ለኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር ከመሆን ባሸገር የከፋ አደጋ ካጋጠማት በኋላም ቢሆን የልማት አጋርነቷ በዓይነትም ሆነ በመጠን አለመቀነሱን ገልጸዋል፡፡

የጃፓን ሕዝብና መንግሥት ከአደጋው ጉዳት ፈጥነው ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚያደንቅ ገልጸው ለአደጋ የማይበገር ማኅበረ-ኢኮኖሚ በመገንባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከችግሩ እንደምተወጣ እምነቴ ነው ብለዋል፡፡

“የበዚህ አጋጣሚ የጃፓን ሕዝብ ከደረሰበት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ለመውጣት ላደረገው ጥረት ያለኝን አድናቆት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡”

በጃፓን የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥና የሱናሚ አደጋ አንደኛ ዓመት ዛሬ በታሰበበት ወቅት በአደጋው ሰለባ ለሆኑ ጃፓናውያን የአንድ ደቂቃ የኅሊና ጸሎት የተደረገ ሲሆን የኃይማኖት አባቶችም መንፈሳዊ የመጽናኛ ቃል ማሰማታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

በአገሪቱ የደረሰው ይህ የተፈጥሮ አደጋ ውስብስብ እንዲሆን ያደረገው የፉኩሺማ የኒኩሌር ማብለያ ጣቢያ በአደጋው ክፉኛ በመጎዳቱ ነበር፡፡

በጃፓን በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥና የሱናሚ አደጋ የደረሰው የኢኮኖሚ ውድመት ከ300 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የተገመተ ሲሆን የጃፓኑ አደጋ በዓለም የአደጋ ታሪክ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ ያስከተለ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡