ሱዳን ለታላቁ ሀዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ድጋፍ ድገፍን አጠናክራ ትቀጥላለች-ፕሬዚዳንት አል በሽር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2004 (ዋኢማ) – ሱዳን በመገንባት ላይ ያለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለሱዳን ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ለስኬቱ አገራቸው ድጋፏን እንደምትቀጥል የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ኦማር አህመድ አል በሽር በሱዳን የኢፌዴሪ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን ሆነው የተሾሙትን የአምባሳደር አባዲ ዘሞ የሹመት ደብዳቤን ሲቀበሉ እንዳሉት የህዳሴው ግድብ መገንባት ለሱዳን ያለው ጠቀሜታ አገራቸው በመገንዘብ ድጋፏን ታደርጋለች።

ኢዜአ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የላከውን መግለጫ ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የህዳሴው ግድብ በታቀደለት የጊዜ ገደብ ተጠናቅቆ የሁለቱ አገሮች የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሱዳን የጀመረችውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው ዘርፈ ብዙ የትብብር ግንኙነትም ከመቼውም ጊዜ ባላይ እየተጠናከረ መምጣቱን ፕሬዚዳንት አልበሽር መናገራቸውን መግለጫው አመልክቷል፡፡

አምባሳደር አባዲ በበኩላቸው ሁለቱ አገሮች በባህል፣ በታሪክና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የዳበረ ትስስር ያላቸውን ትብብር ወደላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር በትጋት እንደሚሰሩ ማረጋገጣቸውን መግለጫውን ጠቅሶ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡

እንደ ኢዜአ ሀገባ ሱዳን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውሉ ከፍተኛ ግምት ያላቸው ከባድ ተሽከርካሪዎችና የግንባታ መሣሪያዎች መለገሷ ይታወሳል።