ሶስተኛው የኢትዮጵያ ብሄራዊ አትላስ በቅርቡ ይፋ ሊደረግ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2/2004 (ዋኢማ) – ሶስተኛው የኢትዮጵያ ብሄራዊ አትላስ በቅርቡ ይፋ እንደሚደረግና ለተጠቃሚዎችም በቅርቡ እንደሚሰራጭ የኢትዮጵያ ካርታ ስራ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሱልጣን መሃመድ ለዋልታ እንደገለጹት ኤጀንሲው  በአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜስን ዘመን ሊሰሩ ለታቀዱት የልማት ስራዎች ተጨማሪ ካርታዎች እያዘጋጀ ነው።

በ1973 የመጀመሪያው በ1981 ደግሞ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ብሄራዊ አትላስ ተዘጋጅቷል። አሁን ደግሞ በያዘው መረጃ ጥልቀት የተሻለ እንደሆነ የተነገረለት ሶስተኛው አትላስ በመዘጋጀት ላይ ነው ።

አዲስ የተዘጋጀው አትላስ የሀገሪቱን የተፈጥሮ፣የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ገጽታ፣ የመሰረተ ልማትና ሌሎች ሀገሪቱ የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ የሚያንጸባርቁ መረጃዎችን አካትቷል።

የአዲስ አበባን 125ተኛ አመት ምክንያት በማድረግም የከተማዋን ሙሉ መረጃ የያዘ አዲስ ካርታ በኤጀንሲው ተዘጋጅቷል። አዲሱ ካርታ ስራ ሲጀምር በተለይ ለቱሪስቶች ስለከተማዋ በቂ መረጃ ይሰጣል።

በተለይ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ለታቀዱት የልማት ስራዎች፣ የየአከባቢዎችን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩ ካርታዎች በኤጀንሲው እየተሰሩ መሆኑንም አቶ ሱልጣን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኤጀንሲው የምስራቅ አፍሪካን የአከባቢ መራቆት መረጃ፣ በየእለቱ ከሳታላይት ይሰበሰባል። ይህም የክፍለ አህጉሩን የተፈጥሮ ሃብት ነባራዊ ሁኔታ ለማጥናትያግዛል።

የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድና የአውሮፓ ህብረት ደግሞ በዚሁ ዘርፍ ከኤጀንሲው ጋር በጋራ በመስራት ላይ ናቸው።

ኤጀንሲው ለየክልል መንግስታት፣ ለአጥኚዎች ፣ ለተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በሚፈልጉት ደረጃ ካርታዎችን እያዘጋጀ እንደሚያቀርብ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።