ባለሥልጣኑ በግማሽ ዓመቱ ከ35 ቢሊዮን ብር በላይ ሰበሰበ

አዲስ አበባ, ጥር 23 (ዋኢማ) – በዘንድሮው ግማሽ የበጀት ዓመት 35 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ምንጮች መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ የሰው ኃይል አደረጃጀቱንና አቅሙንም እየገነባ መሆኑንም ገለጸ፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፋንታ ዛሬ የባለሥልጣኑን የስድስት ወራት የሥራ ክንውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንደገለጹት ገቢው በወቅቱ ለመሰብሰብ የታቀደው 92 በመቶ ግብ ያሳካ ነው፡፡

ገቢው ከአገር ውስጥ ታክስና ታክሰ ካልሆኑ የገንዘብ ምንጮች፣ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ እንዲሁም ከሎተሪ ሽያጭ የተጣራ ትርፍና ከሌሎች ገቢዎች መሰበሰቡን ገልጸዋል፡፡

ገቢው ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የተሰበሰበው ከ10ቢሊዮን ብር በላይ ዕድገት ማሳየቱን የኢ ዜ አ ዘገባ ያስረዳል።

ባለሥልጣኑ የወጪ ንግድን ለማበረታታት ለላኪዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠቱንና በዚህም ከ1ነጥብ 3ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ያስገኙ የአገር ውስጥ ምርቶችን ወደተለያዩ አገሮችና ዓለም አቀፍ ገበያዎች በፈጣን አገልግሎት መላካቸውን አብራርተዋል፡፡

በገቢ ንግድ አፈጻጸም ረገድ ወጪያቸው 84ነጥብ 35 ቢሊዮን ብር ለገቢ ዕቃዎች ሕጋዊ የጉምሩክ የአፈጻጸምሥርዓትን በማለፍ ለአስመጪዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመሰጠት ተናግረዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ሕግ በማስከበር ረገድ በተለይም የአገር ውስጥ የታክስ ሥርዓትን በማጠናከር ሥራን 1ሺህ 289 የግብር ከፋይ የሂሳብ ማህደራት የኦዲት ምርመራ መከናወኑን ገልጸው፣ በዚህም በአጠቃላይ ከ2ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ገቢ እንዳልተከፈለ በምርመራ መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡

በታክስ ስወራና የንግድ ማጭበርበር ሥራ ሁለት ቢሊዮን ብር የመንግሥት ገቢ ዕዳ ከማህደራት የኦዲት ምርመራ በአጋማሽ የበጀት ዓመቱ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

በተጨማረም ከጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ደግሞ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ክፍያ ባለመፈጸሙ ማህደራቸው በተመረመሩ የተቋማትና የንግድ ሰዎች ላይ የግብር ውሳኔ ባለሥልጣኑ ማስወሰኑን ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ የሙያና ክህሎት ክፍተቱን ለመሙላት 2ሺህ 367 የሥራ አመራር አባላትና ፈጻሚዎች ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ ሂደት ላይ መሆኑንና ከሥነ ምግባርና ከሥራ አፈጻጸም አኳያ በተመዘኑ በ2ሺህ 569 ሠራተኞች ላይ በስድስት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሽግሽግና ድልድል መከናወኑን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም በግምገማና ከሌሎች ጠቋሚ አካላት በተገኘ መረጃ 65 አመራር አባላትና ፈጻሚዎች በሥነ ምግባር ጉድለት ከሥራ መሰናበታቸውንም አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡

የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር በጣት አሻራ የማስደገፍ ሥራን ፣የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ አቅርቦት ፣አስተዳደርና ትግበራ ሥርዓትን በማስፋፋት ረገድ ዘመናዊ የጉምሩክ መቆጣጠሪያና መመርመሪያ መሣሪያ ተከላን በተመለከተ የተከናወኑ ዝርዝር ተግባራትን በሪፖርቱ አቅርበዋል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት በገቢና ጉምሩክ አዳዲስ አሰራርና በታዩ ደካማ የአፈጻጸም ስልቶች ላይ በርካታ ቅሬታና ጥያቄዎች ቀርበው ባለሥልጣኑ ችግሮቹን የሚታዩባቸው ሕዝባዊ መድረኮች እየፈጠረ በሂደትም አያሻሻለ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ ቀደም ሲል የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 731/2004ን በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ (ኢዜአ