ኤጀንሲው መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ግዢ እያካሄደ ነው

አዳማ ጥቅምት 24/2004/ዋኢማ/– የኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የጤና ተቋማትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ግዢ በማካሄድ ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡

መድኃኒቶችንና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች በአይነት የመለየትና በመጠን የማስላት የአሠራር ሥርዓትን ለመዘርጋት ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የሦስት ቀናት ዓውደ ጥናት ከትናንት በስቲያ በአዳማ ከተማ ተከፍቷል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለ ሥላሴ ቢሆን ዓውደ ጥናቱን ሲከፍቱ እንደገለጹት፤ በዘንድሮ የበጀት ዓመት የጤና ተቋማትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የሰባት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ግዢ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በ2000 ዓ.ም ዓመታዊ የሀገሪቱ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች በጀት ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አምና ወደ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ዘንድሮ ደግሞ ወደ 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ማደጉን አስረድተዋል፡፡

የአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬታማ የሚሆነውና ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ የሚቻለው ጤንነቱና ደህንነቱ የተጠበቀ አምራች ኃይል ሲኖር ነው ያሉት አቶ ኃይለ ሥላሴ፤ ጥራታቸው ፈዋሽነታቸውና ደህንነታቸው የተሟላ መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች አቅርቦት ሽፋን ለማሳደግ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

«አቅርቦቱ ፍላጎት ተኮር ለማድረግ መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን በዓይነት የመለየትና በመጠን የማስላት መዘርዝር በየጤና ተቋማቱ ሊኖር ይገባል» ያሉት አቶ ኃይለሥላሴ፤ ኤጀንሲው አገልግሎቱን ለማጠናከርና ብክነትን ለመከላከል የ132 መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች በዝርዝር መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የአቅርቦቱን 50 በመቶ እንዲሸፍን ጠቁመው፤ በዓመት በአማካይ 20 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቱ ለማስገባት የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥራና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራች ፋብሪካዎች ከዓለም አቀፍ አምራቾች ጋር ጨረታ ሲወዳደሩ የ25 በመቶ ከለላ፣ የ30 በመቶ የቅድመ ክፍያና የ70 በመቶ ብድር የሚሰጣቸው ከመሆኑም ባሻገር ግብአትን ከውጭ ከታክስ ነፃ እንዲያስገቡ መፈቀዱን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር መንግሥቱ በቀለ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ የተገነቡት 75 የጤና ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸው፤ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ተሟልቶላቸው ኅብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ዓውደ ጥናቱ ገንቢ ሚና ይጫወታል በማለት ኢዜአ ዘግቧል።