የመንግስታቱ ድርጅት ለአፍሪካ ኀብረትና ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት /ኔፓድ/ አቅም ግንባታ ፕሮግራም ድጋፍ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2004/ዋኢማ/– የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአፍሪካ ኀብረትና ለአፍሪካ ልማት አዲስ አጋርነት /ኔፓድ/ አቅም ግንባታ ፕሮግራም ተፈፃሚነት ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

በአፍሪካ ኀብረትና በኔፓድ ፕሮግራም ድጋፍ ዙሪያ የሚሰሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ተቋማት 12ኛው አህጉራዊ የትብብር ማዕቀፍ ጉባዔ ዛሬ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ ተከፈተ።

የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ፀሐፊ ዶክተር አሻሮዝ ሚጊሮ በጉባዔው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ተቋማት የአፍሪካ ኀብረትን ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም አላቸው።

እንዲሁም አፍሪካ የሚሌኒየም የልማት ግቦች እንድታሳካ ብሔራዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የገንዘብ ዕገዛ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲመቻች ይደረጋል ብለዋል።

አህጉራዊ የትብብር ማዕቀፍ ልምድ እንዲዳብር ተመሳሳይ ተቋማት እንዳይከፈቱ በማድረግ አህጉራዊ የትብብር ግንኙነትን ማረጋገጥ እንደሆነም አመልክተዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2006 የአስር ዓመት የአፍሪካ ኀብረት አቅም ግንባታ ፕሮግራም የተነደፈ ሲሆን፤ ፕሮግራሙ ውጤታማ ተፈፃሚነት እንዲኖረው ተቋማቱ ጠንክረው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን አቅምን ማሳደግ፣ የአፍሪካ ክፍለ አህጉራዊ ድርጅቶች ከተባበሩት መንግስታት ጋር ውጤታማ ተግባራትን በማከናወን በአፍሪካ ልማት ላይ ለተጋረጡት ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ሚስተር ኢራስተስ ምዌንቻ እንደገለጹት፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ተቋማት ለአፍሪካ ሰላም፣ ፀጥታና ልማት ፕሮግራም ማስፈጸሚያ በርካታ ሃብት በማፈሰስ ላይ ይገኛሉ።

በአፍሪካ ልማት ላይ የተጋረጡ ተግዳሮቶችን ምላሽ ለመስጠት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ተቋማት ለሚያደርጉት ድጋፍ የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን እንደሚያመሰግን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን አቅምን ማሳደግ አህጉራዊ የትብብር ማዕቀፍ የሚጫወተው ሚና ወሳኝ እንደሆነም ሚስተር ምዌንቻ አስረድተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ተቋማትና የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን ለአፍሪካ አገራት ልማትና ዕድገት ተመሳሳይ አቋም እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ሚስተር አብዱላሂ ጃኔ በበኩላቸው ለአፍሪካ ኀብረት አቅም ግንባታ ፕሮግራም በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ተቋማት በኩል ተግባራዊ የሚደረገው አህጉራዊ የትብብር ማዕቀፍ ወሳኝ እንደሆነም ገልጸዋል።

የአቅም ግንባታ ፕሮግራሙ አፍሪካ የሚሌኒየም የልማት ግቦች እንድታሳካ ከፍተኛ ዕገዛ የሚያደርግ መሆኑንም አብራርተዋል።

በብራዚል ሪዮ ዲጄኔሪዮ ከተማ በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ጉባዔ ላይ አፍሪካውያን አንድ ድምፅ ለማሰማት በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ለሁለት ቀናት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ የሚካሄደው 12ኛው አህጉራዊ የትብብር ማዕቀፍ ጉባዔ ላይ የአስር ዓመት የአፍሪካ ኀብረት አቅም ግንባታ ፕሮግራም ተግባራዊ ለማድረግ በቀረበ ረቂቅ የሥራ ፕሮግራም ላይ ውይይት ይካሄዳል።

በተጨማሪም የአፍሪካ የሚሌኒየም የልማት ግቦች የሥራ ቡድን ወቅታዊ ማድረግ፣ በሪዮ ዲጄኔሪዮ ከተማ ለሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባዔ አህጉራዊ ዝግጅት፣ አህጉራዊ የትብብር ማዕቀፍ በአፍሪካ አካባቢ ጥበቃ፣ ሥነ ሕዝብና የከተሞች ትስስር ላይ ሰፊ ምክክር የሚደረግ መሆኑን የዘገበው ኢዜአ ነው።