የተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን የመድህን ዋስትና ምዝገባ ህዳር 30 እንደሚጠናቀቅ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/ 2004/ዋኢማ/– የተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን የመድን ዋስትና ፈንድ ምዝገባ በተያዘው ወር መጨረሻ ላይ የሚጠናቀቅ በመሆኑ ማንኛውም ተሽከርካሪ ወደየመድህን ሰጪ ኩባንያዎች በመሄድ እንዲመዘገብ የመድህን ፈንድ ጽህፈት ቤት አሳሰበ።

የጽሕፈት ቤቱ ተወካይ አቶ ሲሣይ አባፈርዳ በሰጡት መግለጫ፤ ማንኛውም ተሽከርካሪ እስከ ህዳር 30 ቀን 2004 ዓ.ም ድረስ ወደ መድህን ሰጪ ኩባንያዎች በመሄድ ካልተመዘገበ ወደ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ሁሉም ተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን ኢንሹራንስ እንዲገቡ ቀደም ሲል ጥሪ የቀረበ ቢሆንም የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ፈጥነው ተግባራዊ ከማድረግ ይልቅ ዛሬ ነገ በማለት መጓተት እያሳዩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም የጊዜ ገደቡ እስከ ህዳር 30 ቀን ብቻ በመሆኑ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ወደሚፈልጉት የመድህን ሰጪ ኩባንያ በመሄድ እንዲመዘገቡ ያሳሰቡ ሲሆን፤ ቀደም ሲል የሶስተኛ ወገን መድን የነበራቸውም ውላቸውን ማስተካከል እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

በአለም ላይ በተሽከርካሪዎች በሚደርስ የትራፊክ አደጋ ምክንያት በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ያላነሱ ሰዎች የሚሞቱ ሲሆን፤ ከ20 ሚሊየን በላይ ደግሞ ለአካል ጉዳት ይዳረጋሉ።

በሀገራችን በኢትዮጵያም በአመት በአማካኝ ወደ 11ሺ የሚጠጉ ሰዎች ለሞትና ለአካል ጉዳት የሚጋለጡ ሲሆን፤ በርካታ ንብረት እንደሚጠፋ ይታወቃል።

የሶስተኛ ወገን የመድህን ዋስትና መግባት ያስፈለገውም በአገሪቱ በተሽከርካሪዎች አደጋ ምክንያት በሶስተኛ ወገን ላይ የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በማስወገድ ደህንነቱ የተጠበቀ ህብረተሰብ ለመፍጠር ነው።

መንግስትም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ የሶስተኛ ወገን የመድን ዋስትና አዋጅ ይገኝበታል።

የተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን የመድን ዋስትና በአዋጅ ቁጥር 559/2000 የተደነገገ ሲሆን፤ ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ተወካዩ ገልፀዋል።

የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ደንበኞችን በአግባቡ ማስተናገድ እንደሚገባቸው አሳስበው፤ አንዳንድ ኩባንያዎች ተሽከርካሪዎችን እየመረጡ ማስተናገድና መንግስት ከወሰነው ታሪፍ ውጭ ማስከፈልና የመሳሰሉ ችግሮች እንዳሉ መረጃዎች ጽህፈት ቤቱ እንዳለውም ተናግረዋል።

በመሆኑም ማንኛውም የመድህን ሰጪ ኩባንያ፣ ባለተሽከርካሪዎችና ህብረተሰቡም የአዋጁን አላማ በመረዳት ተባባሪ መሆን ይገባቸዋል በማለት ገልፀዋል።

በሂደት ላይ የሚከሰቱ ችግሮች ሲያጋጥሙም ህብረተሰቡ ለጽህፈት ቤቱ ጥቆማ  በማድረግ ለአዋጁ ተግባራዊነት የበኩሉን በመጫወት በሶስተኛ ወገን የመድህን ዋስትና ሌሎች አገሮድ የደረሱበት ለመድረስ ተባብረን መስራት ይኖርብናል ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።