የከሰም ስኳር ፋብሪካን ለመገንባት የሚያስችል የግንባታ ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ ህዳር 8/2004/ዋኢማ/– የከሰም ስኳር ፋብሪካን ለመገንባት የሚያስችል የግንባታ ስምምነት በስኳር ኮርፖሬሽን ፣ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እና ኮምፕላንት በተሰኘ የቻይና ኩባንያ መካከል ተፈረመ፡፡

ስምምነቱን የፈረሙት በሚኒስትር ማዕረግ የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ አባይ ጸሐዬ፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኮሌኔል ጠና ቁሩንዴ እና የኮምፕላንት ኩባንያ የስራ ኃላፊ ሚስተር ማ ማኦዚያን ናቸው፡፡

የስኳር ኮርፖሬሽን በስኳር ልማት ዘርፍ ለማከናወን በያዘው የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅድ መሰረት ከሚያስገነባቸው አስር አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሆነውን የከሰም ስኳር ፋብሪካን ለመገንባት የሚያስችለው የ150 ሚሊዮን ዶላር የፋይናንስ ፍላጎት ከቻይና ልማት ባንክ በሰኔ ወር 2003 ዓ.ም በብድር ተገኝቷል፡፡

አሁን በተፈረመው ስምምነት መሰረት ደግሞ የፋብሪካውን ግንባታ፣ የማሽነሪ ተከላውንና ሌሎች የሲቪል ስራዎችን የሚያከናውነው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ነው፡፡

በተጨማሪም ስምምነቱ መንግስት የአገር ውስጥ አቅምን ከማጎልበት አንጻር የሚከተለውን አቅጣጫ መሰረት ያደረገ ሲሆን፤ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የፋብሪካ ግንባታውን ስራ ሙሉ በሙሉ እንዲያከናውን እና የዲዛይን ስራውን ከኮምፕላንት ኩባንያ ጋር በጋራ እንዲሰራ የሚያስችለው ነው፡፡

ኮምፕላንት የተሰኘው ኩባንያ ለከሰም ስኳር ፋብሪካ ግንባታ የሚያስፈልጉ የፋብሪካ አካላትን ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የማቅረብ እና የዲዛይን ስራውን ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የማከናወን የስራ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የሚገነባው የከሰም ፋብሪካ ሲጠናቀቅና በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በቀን አስር ሺህ ቶን አገዳ በመፍጨት በአመት 250‚000 ቶን ስኳርና 20‚000 ሜትር ኩብ ኤታኖል የማምረት አቅም እንደሚኖረው ኢሬቴድን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።