ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የዛምቢያ አምባሳደር አሰናበቱ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2004/ዋኢማ/ – ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በኢትዮጵያ የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የዛምቢያ አምባሳደር አሰናበቱ፡፡

ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዩርጊስ ትናንት በጽህፈት ቤታቸው አምባሳደሩን ባሰናበቱበት ወቅት እንዳሉት ሁለቱ አገራት በተለያዩ መስኮች የሚያደርጉትን ትብብር ለማጠናከር የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

በተለይም በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ መረጃዎችን በመለዋወጥ፣በማዕድንና በትምህርት እንዲሁም በተለያዩ መስኮች በጋራ እንዲሰሩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራም ተሰርቷል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዛምቢያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ የምትቀጥል ሲሆን የኢትዮጵያና የዛንቢያ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ለማቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡

አምባሳደሩ አልበርት ኤም ሙቺንጋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ዛምቢያና ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መስኮች በትብብር እየሰሩ ናቸው፡፡

በተለይም ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ፕሬስ ድርጅቶች ጋር የሁለቱ አገራት ዜና አገልግሎቶች መረጃን የመለዋወጥ ተግባራትን እንዲያካሄዱና በትብብር እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችል ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የዛምቢያ ዩኒቨርስቲዎች በትብብር ሊሰሩ የሚችሉበት መንገድ እየተመቻቸ ሲሆን በተጨማሪም በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍም በጋራ እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም በቀንድ ከብት ልማትና በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ስራ ለመስራት ያቀዱ ሲሆን፤ በሆቴልና በሌሎች የንግድ መስኮች ልማትም በትብብር እንደሚሰሩ መጠቆማቸውን የኢዜአ ዘገባ ያስረዳል።