የጅጅጋ ዩኒቨርስቲ የብአዴን አባል ተማሪዎችና የከተማው ነዋሪዎች የብአዴንን 31ኛ የምስረታ በዓል አከበሩ

ጅጅጋ፤ ህዳር 19/2004/ዋኢማ/-የጅጅጋ ዩኒቨርስቲ የብአዴን አባል ተማሪዎችና የጅጅጋ ከተማ ነዋሪዎች በተለያዩ ተግባራት የብአዴንን 31ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በድምቀት አከበሩ፡፡

ጅጅጋ ዩኒቨርስቲ የብአዴን አባል ተማራዎችና የጅጅጋ ከተማ የድርጅቱ አባላት ከትላንት በስቲያ የብአዴንን 31ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ባከበሩበት ወቅት የጅጅጋ ከተማ የብአዴን አስተባባሪ አቶ ክንዴ ገበየሁ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የተጀመሩትን የልማት፣ መልካም አስተዳዳርና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይበልጥ ለማጠናከር አባላቱ የላቀ ተሳትፎ ይጠበቅበታል፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ትላልቅ የልማት ውጥኖችን በመዘርጋት የእድገትና የትራንስፎርሜሽኑን እቅድ ለማሳካት በምታደርገው ጥረት የብአዴን አባላትና ደጋፊዎች በግምባር ቀደም በንቃት ሊሳተፍ እንደሚገባ አሳስበው፤ ብአዴን ባለፋት ዓመታት ባካሄዳቸው ትግል የክልሉን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግቧል ብለዋል፡፡

በሶማሌ ክልል የሚገኘው የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎችም በክልሉ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች በመሳተፍ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ አሁንም አባላቱ ባሉበት አካባቢ የተሻለ ስራ በመስራት ለአገር የሚጠቅም ተግባራት ማከናውን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የጅጅጋ ዩኒቪርሲቲ ተማሪዎች የብአዴን አስተባባሪ ወጣት ፍሰሃ አለሜ በበኩሉ እንደተናገረው፤ ወጣት የብአዴን አባል ተማሪዎች በትምህርታቸውና በስራቸው ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን አገሪቱ ከነሱ የምትጠብቀውን ለማበርከት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡

ተማሪዎች ራሳቸውን ከአልባሌ ቦታና ከተለያዩ ሱሶች በመጠበቅ በትምህርታቸው በርትተው በማጥናት ነገ የተሻለ የሀገር ተረካቢ ለመሆን መስራት እንዳለባቸውም አሳስቧል።

የብአዴንን 31ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በመድረግ አባላቱና ደጋፊዎች በጂጂጋ ከተማ ለሁለት ቀናት የጽዳት ዘመቻና ውይይት ማካሄዳቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡