የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2004/ዋኢማ/ – የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዓመታዊ ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ተካሄደ።

የጋራ ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው ስብሰባ በተለያዩ አገራዊ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ ደርሷል።

ውይይት ከተደረገባቸው አጀንዳዎቹ መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በሙሉ ድምጽ ተስማምተዋል።

በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚከፈቱት የጋራ ምክር ቤቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች የመደመጥ መብትን የሚያጠናክርና ከክልል ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል በመሆኑ በጋራ ምክር ቤቱ አባላት ስምምነት ላይ ተደርሷል።

የጋራ ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በመገናኛ ብዙሃን ውይይት ለማድረግ ያሳለፈው ውሳኔ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲሆንም ተስማምተዋል።

በቀጣይ ተግባራዊ በሚደረጉ ጉዳዮች ላይም የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ሰፊ ምክክር ያደረጉ ሲሆን ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን የሚያካሂዷቸው ውይይቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የውይይት ባህሉ እንዲዳብርም ተስማምተዋል።

ዛሬ በተካሄደው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዓመታዊ ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ኢህአዴግ፣ ኢዴፓ፣ ቅንጅት፣ ኢፍዴኃግ፣ ኢራፓ፣ ኢሰዴፓና መኢብን ተካፍይ መሆናቸውን የኢዜአ  ዘገባን ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።