አምቦ፤ ህዳር 20/2004/ዋኢማ/– የፊንጫን ስኳር ፋብሪካ ለማስፋፋት ግማሽ ቢሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ እየተገነባ ያለዉ የመስኖ ማስፋፊያ 86 በመቶ መጠናቀቁን በፌዴራል የዉኃ ስራዎች ኮንስራክሽን ድርጅት የፕሮጀክቱ ኢንጂነር ገለጹ።
ኢንጂነር አሸናፊ አያሌዉ እንደገለፁት፤ ሰባት ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የታቀደው ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት አምስት ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ የአገዳ ተክል ማልማት የሚያስችል ዉሃ ደርሷል።
ቀሪዉን መሬትም በአገዳ ተክል መሸፈን እንዲቻል ዉሃ ለማድረስ የቧንባ መስመር መዘርጋት ስራ በማፈጠን ላይ መሆኑን ገልጸው፤ አላማዉ በመንግስት የተነደፈዉን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በስኳር ልማት ዘርፍ የተያዘዉን እቅድ ለማሳካት መሆኑንም አስታውቀዋል።
በፕሮጀክቱ 40 ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የመስኖ ዉሃ ኮንክሪት ካናል ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መጀመሩን ገልጸው፤ ወደ አገዳ ተክሉ ማሳ የሚያደርሰዉ የ69 ኪሎ ሜትር ዋናና መጋቢ መንገዶች ስራ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል ሰባት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በሙሉ አቅሙ አገዳ ያለማ የነበረዉ ፋብሪካዉ አሁን በዉሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የሚገነባዉ የመስኖ ፕሮጀክት በየካቲት 2004 ስራዉ ሲጠናቀቅ የፋብሪካዉን የማምረት አቅም ከእጥፍ በላይ እንደሚያሳድገዉ አስታዉቀዋል።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሺህ የሚበልጥ የአካባቢዉ ስራ አጥ ወገኖች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል የፈጠረላቸዉ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያስረዳል።
ድርጅቱ በተያዘዉ በጀት አመት የሞጆ ደረቅ ወደብን፣ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካን ህንጻና መጠጥ ዉሃ ግንባታ በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለማስረከብ ጥረቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።