የኢትዮጵያ ከተሞች በህዳሴ ጎዳና በሚል የከተሞች ሳምንት ትናንት በመቀሌ ከተማ መከበር ጀመረ


መቀሌ፤ ህዳር 20/2004/ ዋኢማ/-
ከተሞች የኢንቨስትመንት መዳረሻና የዘመናዊ አስተዳደር መገለጫዎች እንዲሆኑ ከማድረግ በተጨማሪ አገራችን ኢንዱስትሪ በማስፋፋትና ባለቤትና ጠንካራ የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸዉን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አስታወቁ ።

”የኢትዮጵያ ከተሞች በህዳሴ ጎዳና” በሚል መሪ ቃል የከተሞች ሳምንት ትናንት በመቀሌ ከተማ መከበር ጀመሯል።

አፈ-ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለብርሃን በበአሉ ላይ እንደገለፁት በዓሉ የአገራችን ገፅታን ለመቀየርና በከተሞች መካከል ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር የሚኖረው ድርሻ የላቀ ነዉ።

ከተሞቻችን ህዝብን ያሳተፈ የልማት እንቅስቃሴዎች በስፋት የሚታይባቸው፣ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎችና በጠንካራ ኢኮኖሚ ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ልማት የሚካሄድባቸዉ እንዲሆኑ የተያዘዉ ጥረት ዉጤት እያስገኘ ነዉ ብለዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ በበኩላቸው፤ አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር ጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ተቋማት አደራጅቶ ወደ ስራ በማስገባት በከተሞች የማይናቁ ሰፊ ተግባሮች መከናወናቸዉን አስታዉቀዋል።

በከተሞች የመልካም አስተዳደር ጉድለት ሲታይበት የቆየውን የመሬት ልማትና አስተዳደር ችግር ለማስወገድ የማስተካከያ እርምጃዎች ከመወሰዳቸው በተጨማሪ የዘርፉን አመራር ፍትሃዊና ግልፅ በሆነ የአሰራር ፖሊሲ እንዲመራ የሚያስችል ስትራቴጂ እንዲቀረፅለት መደረጉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከትምህርት ሚኒስቴርና ከቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ከስልጠና ተቋም በመተባበር ለመሬት ልማትና ስራ አመራር የሚያስፈልጉ ስልጠናዎች መካከለኛ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አስታዉቀዋል።

ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በመስኩ የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ስርዓተ ትምህርት/ካሪክለም/ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በዓሉ በከተማ ልማት ስራዎች ያሉትን መልካም ተሞክሮዎች በመቀመርና የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ የሚያግዝ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ ህዝብ፣ መንግስትና ባለሃብቶች ተቀናጅተው በልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጎለብቱ ያስችላቸዋል ብለዋል።

እንዲሁም በከተሞች መካከል የልምድ ልውውጥና መልካም የውድድር መንፈስ በመፍጠር የተሻለ እድገት ለማስመዝገብ በጎ ገፅታቸውን ለማስተዋወቅ የሚያግዝ ከመሆኑም ሌላ በየከተሞቹ የሚገኙ ነዋሪዎች ለልማት እንዲነሳሱ እንደሚያደርግ አቶ መኩሪያ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው፤ በዓሉ በከተማ ስራዎቻችን የሚታዩ ምርጥ ተሞክሮዎች መነሻ በማድረግ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል።

የጥቃቅንና አነስተኛ የልማት ተቋማት አገራችን ለቀየሰችው የኢንዱስትሪ ልማት መሰረት መሆናቸው በማመን በመንግስት እየተደረገላቸው ያለውን ድጋፍና ክትትል የማጠናከሩ ስራ በዋነኛነት የከተሞቹ አመራሮች ተግባር መሆኑን አውቀው በትኩረት ሊንቀሳቀሱ ይገባል ብለዋል።

ለሶስተኛ ጊዜ መከበር በጀመረውና ለስድስት ቀናት በሚቆየዉ የከተሞች ሳምንት በዓል ላይ 122 ከተሞች እና 15 የልማት ተቋማት የተሳተፉ ሲሆን፤ በመካከላቸው ውድድር የሚካሄድ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በበዓሉ ላይ የከተሞቹ የልማት ስራዎች የሚያሳይ ኤግዚብሽን በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና በክልሉ ርእሰ መስተዳድር ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን፤ የክብር እንግዳውና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ስራዎቹን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን የኢዜአ ዘገባ ይገልፃል።

በተጨማሪም በየከተሞቹ የሚታየው የመሬት ልማትና አስተዳደር፣ አነስተኛና ጥቃቅን የንግድ ተቋማት ለማበረታት እየተደረጉ ያሉት ጥረቶችና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ከነገ ጀምሮ ውይይት የሚካሄድ መሆኑን ለበዓሉ ከተዘጋጀው ፕሮግራም ለመረዳት ተችሏል።