በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 11 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር አዲስ እርዳታና ብድር ተገኘ

 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2004/ ዋኢማ/ – በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከመልቲ ላተራልና ባይላተራል ምንጮች ከውጭ ሀብት ግኝት 11 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር አዲስ እርዳታና ብድር፣ 11 ቢሊዮን ብር ደግሞ የእርዳታና ብድር የገንዘብ ፍሰት መገኘቱን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።  ኢትዮጵያ በሩብ አመቱ ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ የእዳ ቅነሳ ተጠቃሚም ሆናለች፡፡

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኢንፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ ትናንት የ2004 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የውጭ ሀብት ግንኙነትና ፍሰትን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ከመልቲ ላተራል ምንጮች 2 ነጥብ 58 ቢሊዮን፣ ከባይላተራል ምንጮች ደግሞ 9 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ከውጭ ሀብት ግኝት ሊገኝ ችሏል ብለዋል።

በገንዘብ ፍሰት ረገድም በ2004 የመጀመሪያ ሩብ አመት ለፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈፀሚያ ከሁለቱ ምንጮች 11 ቢሊዮን ብር የእርዳታና የብድር ፍሰት መገኘቱን ገልፀዋል፡፡

የገንዘብ ፍሰቱ ካላፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፃር የ952 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

የእርዳታና ብድር የገንዘብ ግኝትና ፍሰቱ ካላፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ሊጨምር የቻለው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን አስመልክቶ ውጪ ላሉ ኢትዮጵያውያንና ለጋሾች ገለፃ ተደርጐ መግባባት ላይ በመደረሱ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእዳ ጫና ያለባቸው ደሃ አገሮች የእዳ ማቃለያ ፕሮግራም ተጠቃሚ ከመሆኗ በተጨማሪ የቡድን ስምንት አባል ሀገራት የእዳ ማቃለያ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንደሆነችም አመልክተዋል።

ሀገሪቱ ለዕድገት ካላት ራዕይና ከድህነት ለመውጣት ካሳየችው ጥረት በመነሳት በ2004 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ54 ሚሊዮን ብር በላይ የእዳ ቅነሳ ተጠቃሚ መሆኗን አስታውቀዋል።

የዕዳ ቅነሳ ያደረጉ ለጋሽ ድርጅቶችም የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ መሆናቸውን የኢዜአ ዘግቧል።