ሁለተኛው ዙር የተንዳሆ ቤቶች ልማት ግንባታ 98 በመቶ መጠናቀቁ ተገለፀ

አዲስ አበባ ህዳር 22/2004/ዋኢማ/ – በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት በመገንባት ላይ ያለው ሁለተኛው ዙር የቤቶች ልማት ግንባታ 98 በመቶው መጠናቀቁ ተገለፀ።

የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ ሀበነ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤  እየተካሄደ ያለው ሁለተኛው የቤቶች ልማት ግንባታ በመጪው ታህሳስ ወር ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል።

በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ አስራ ሁለት መንደሮችን ለመገንባት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን የገለፁት አቶ ምትኩ፤ በአሁኑ ወቅት 9ሺ 15 የመኖሪያ ቤቶችና 146 ማህበራዊ ተቋማትን በመገንባት የተለያዩ ደረጃዎች ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የቤቶቹን ግንባታ በሁለት ምዕራፍ በመክፈል የተካሄደ ሲሆን፤ ለሁለቱም ምዕራፍ ሁለት ቢሊየን ብር ወጪ እንደተደረገም ተናግረዋል።

በስራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር በ1999 ዓ.ም የተጀመረው የመጀመሪያው ዙር ግንባታ 338 የሚኖሪያ ቤቶችና 61 ማህበራዊ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቅ ላይ ያለው ሁለተኛው ምዕራፍም 5 ሺ 628 የመኖሪያ ቤቶችና 85 ማህበራዊ ተቋማት ግንባታቸው 98 በመቶው መጠናቀቁን ገልፀዋል።

በግንባታውም ከ300 በላይ የስራ ተቋራጮች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከነዚህም መካከል ሰባዎቹ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ስራ የገቡ የክልሉ ተወላጆች መሆናቸው ተገልጿል።

በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበር ተደራጅተው በግንባታው ከተሳተፉት 280 አባላት 168 የሚሆኑ ፕሮጀክቱ የክልሉን ተወላጆች በማደራጀት የቴክኖሎጂው ሽግግርና የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረጉ ነው ብለዋል።

በፕሮጀክቱ ከተሳተፉ ማህበራት መካከል የደበልና ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ሞሚን መሀመድ እንደገለፀው፤ ፕሮጀክቱ ባደረገላቸው የ15 ሺ ብር ድጋፍ ስራውን መጀመራቸውንና በአሁኑ ወቅት የማህበሩን  ካፒታል ወደ 150 ሺ ብር ማሳደግ መቻሉን ተናግሯል።

በገንዘብ የማይተመን የተለያዩ የሞያ ክህሎቶች እንደቀሰሙም ወጣቱ በመግለፅ በቀጣይ በክልሉ በሚካሄዱ የግንባታ ዘርፎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከትም ፍላጎት እንዳላቸው ገልጿል።

ከግንባታ የስራ ዘርፎች መካከል ከ2 ሚሊየን ብር በላይ ኮንትራት በመፈራረም የተለያዩ ስራዎችን ያከናወነችው የአፋር ክልል ተወላጅ ወይዘሮ መሪየም ሀሰን በበኩሏ ፕሮጀክቱ የስራ እድል በመፍጠሩ በኑሮዋ ለውጥ ማምጣት መቻሏን ማስረዳቷን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።