ህብረተሰቡ የደም ምርመራ በማድረግ እራሱን እንዲያውቅ ተጠናክሮ ሊሰራ ይገባል

አዲስ አበባ ህዳር 22/2004/ዋኢማ/– “አንድም ሰው በኤችአይቪ እንዳይያዝ፣ እንዳይገለልና እንዳይሞት ኃላፊነታችንን እንወጣ” የሚለውን የዘንድሮውን የዓለም የኤድስ ቀን መሪ ቃል ለማሳካት አጠቃላይ ህብረተሰቡ የደም ምርመራ በማድረግ እራሱን እንዲያውቅ ተጠናክሮ መሰራት እንደሚገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አሳሰበ።

የቢሮው የቲቢና ኤችአይቪ ኦፎሰር ሲስተር ሰናይት አሰፋ ትናንት የዓለም የኤድስ ቀንን ምክንያት በማድረግ  ኔትወርክ ኦፍ ኔትወርክስ ኦፍ ኤችአይቪ ፖዘቲቭስ ኢን ኢትዮጵያ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንደገለፁት፤ ህብረተሰቡ የደም ምርመራ በማድረግ እራሱን እንዲያውቅም ቁልፍ የሆነውን የመከላከልና የመቆጣጠር ስልቶችን በማጠናከር፣ አገልግሎቶችን በማስፋትና በጥራት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ማድረስ ይገባል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮም የአመቱን መሪ ቃል መሰረት በማድረግ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትንና የከተማውን ህብረተሰብ በማስተባበር ተልዕኮውን ለመወጣት ዝግጅቱን አጠናቆ በትግበራ ላይ እንደሚገኝ ሲስተር ሰናይት ተናግረዋል።

እንዲሁም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የሚሰጠውን የምክርና የደም ምርመራ በማጠናከር አንድም ህፃን ከቫይረሱ ጋር እንዳይወለድ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግም ገልፀዋል።

የኔትወርክ ኦፍ ኔትወርክስ ኦፍ ኤችአይቪ ፖዘቲቭስ ኢን ኢትዮጵያ ድርጅት የአድቮኬሲ፣ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ክፍል ስራ አስኪያጅ አቶ ጥጋቡ አስረስ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ የቫይረሱ ስርጭት ዜሮ እስኪሆን ድረስ በመከላከል፣ በመንከባከብና ድጋፍ በማድረግ ላይ ትኩረቱን አጠናክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች ያቋቋሟቸውን ማህበራት በማሰባሰብ የማስተባበር ስራ በመስራት ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ስራውን ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠልም ከ11 ክልሎችና አስተዳደሮች፣ ከሶስት ብሔራዊ ማህበራት፣ ከሀብኮና ከሌሎች መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምንት ላይ መድረሱንም አስታውቀዋል።

ድርጅቱ በሚቀጥሉት አመታት ስራውን ይበልጥ አጠናክሮ ለመስራትም ከሲዲሲና ከግሎባል ፈንድ 50 ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቱን ጠቁመው፤ በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖች ማህበራትን ለመርዳትና በተለይም በምግብ እጥረት መድሃኒቱን የሚያቋርጡ ወገኖችን ለመርዳት መታቀዱን ገልፀዋል።  

በአጠቃላይ በሀገሪቱ በተካሄደ ሰፊ እንቅስቃሴ በኤችአይቪ/ኤድስ ላይ እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ውጤት ማሳየቱን ጠቁመው፤ የተጀመረውን ጉዞ አጠናክሮ በመቀጠል የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ማሳደግ ይገባል ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።