በነገው ዕለት የሚጀመረው 16ኛው ዓለም አቀፍ የኤችአይቪ/ኤድስና አባላዘር በሽታዎች በአፍሪካ ጉባዔ ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ

አዲስ አበባ ህዳር 23/2004/ዋኢማ/-በነገው ዕለት በሚሊኒየም የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚጀምረው 16ኛው ዓለም አቀፍ የኤችአይቪ/ ኤድስና አባላዘር በሽታዎች በአፍሪካ ጉባዔ ዝግጅት መጠናቀቁን የጉባዔው አዘጋጅ “አይካሳ” አስታወቀ።

የአይካሳ የኮሙኒኬሽንና የማስታወቂያ ክፍል ስራ አስኪያጅ አቶ ሚኪያስ ሲሳይ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ጉባዔው የሚካሄድበትን የሚሊኒየም አዳራሽ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የማደራጀት ስራ፣ እንግዶች የሚያርፍባቸውን ሆቴሎች የመምረጥ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የማመቻቸትና ሌሎች ሥራዎች ተጠናቀዋል።

እንዲሁም የተለያዩ አውደ ርዕይ የሚታዩባቸው ቦታዎች፣ በየክፍሎች ያሉ መብራቶችና ሌሎች ዝግጅቶች በተፈለገው ሁኔታ መሰራታቸውን የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአውደ ርዕዩ የሚሳተፉ ወገኖች እቃዎቻቸውን እያስገቡ መሆናቸውን ጠቁመው፤ አንዳንድ እንግዶችም በመግባት ላይ ናቸው ብለዋል።

የአይካሳ የበላይ ጠባቂን ጨምሮ ሌሎች እንግዶችም ወደ አዲስ አበባ እየገቡ መሆናቸውን ገልፀው፤ ብረተሰቡም የቆየ የኢትዮጵያ ባህል የሆነውን እንግዳ ተቀባይነት በተግባር በማሳየት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ማሳሰባቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።