ባለሥልጣኑ የግንባታ ጥራት መፈተሻ ቤተ-ሙከራ አቋቋመ

ሀዋሳ፤ ህዳር 27/2004/ዋኢማ/ – የደቡብ ክልል የዲዛይንና የግንባታ ቁጥጥር ባለስልጣን የግንባታ ጥራት ቁጥጥርን በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችለውን የግንባታ ጥራት መፈተሻ ቤተ-ሙከራ ማቋቋሙን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ማርቆስ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቁት፤ የግንባታ ጥራት መፈተሻ ቤተሙከራው መቋቋም በክልሉ በመካሄድ ላይ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ባለሥልጣኑ በሚያወጣው መመዘኛና መስፈርት መሠረት መከናወናቸውን ለመቆጣጠር ያስችላል።

የመፈተሻ ቤተ-ሙከራው በዓለም አቀፍ ደረጃ የግንባታ ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ዘመናዊ የጥራት መፈተሻ መሣሪያዎች ያሟላ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ  የግንባታ ጥራት ፍተሻ ለማከናወን  ናሙናዎችን አዲስ አበባ በመላክ ለጊዜ ብክነትና ለተጨማሪ ወጪ ሲዳረግ መቆየቱን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት ግን ባለሥልጣኑ የራሱን የግንባታ ጥራት መፈተሻ ቤተ ሙከራ በማቋቋሙ ችግሮቹ ሙሉ ለሙሉ መቀረፉን አብራርተዋል።

የግንባታ ጥራት መፈተሻ ቤተ ሙከራው በክልሉ እያደገ የመጣውን የግንባታ ዘርፍ ጥራትን ማስጠበቅ ከማስቻሉም በላይ በመንግሥትና በግል ባለሀብቶች መገንባት ላይ የሚገኙ የመሠረተ ልማቶች ደረጃጀውን የጠበቁና ረጅም የአገልግሎት ዘመን እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሚረዳ አስረድተዋል።

ከተያዘው የበጀት ዓመት መግቢያ ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የግንባታ መፈተሻ ቤተ ሙከራ የተገነባው የክልሉ መንግሥት በመደበው የ2 ሚሊዮን ብር ወጪ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። 

ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በደቡብ ክልል በአሁኑ ወቅት ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አሥር ፍቃድ ያላቸው 302 የግንባታ ሥራ ተቋራጮች በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው።

ተቋራጮቹ ከተለያዩ የክልሉ አሥፈጻሚ ቢሮዎች ጋር ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የግንባታ ውሎችን በመግባት የመንገድ፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ግንባታን ጨምሮ 563 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።