በኤርትራ ላይ የተጣለው ማእቀብ አለም የኢሳይያስ አፈወርቂ መንግስት በድጋሚ ፀረ ሰላም መሆኑን ያረጋገጠበት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 28/2004/ ዋኢማ/ – የጸጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ያስተላለፈው ማእቀብ አለም በአንድ ድምጽ የኢሳይያስ አፈወርቂ መንግስት በድጋሚ ፀረ-ሰላም መሆኑን ያረጋገጠበት መሆኑን የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ እንዳሉት የኤርትራ መንግስት የማተራመስ ድርጊቱን የማይተው ከሆነ የፀጥታው ምክር ቤት በ3ኛ ዙር ሊያደርግ በሚችለው ጉባኤው የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ የሚያስችል አቅጣጫ አስቀምጧል።

ማእቀቡ ለኤርትራ መንግስት አለም በአንድ ድምጽ ኤርትራ ፀረ-ሰላም መሆኗን እና ህዝቡ መንግስታቸው አደብ እንዲገዛ የሚል መልክት ያስተላልፋል ብለዋል።

አልሸባብን እየረዳ አለም እንዳይረጋጋ ማድረጉ የተረጋገጠበት የኤርትራ መንግስት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የሚጠብቀው እድል  መለወጥ ወይም መጥፋት ብቻ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ያምናል ብለዋል።

ማዕቀቡ ተግባራዊ እንዲሆን የኢጋድ አባል ሃገራት የተባበሩት መንግስታት ላቋቋመው ተቆጣጣሪ ቡድን በየጊዜው የሚፈጠረውን ክስተት ሪፖርት በማድረግ የክትትል ስራቸውን ለማጠናከር መምከሩን ተናግረዋል።

በስምምነቱ ወቅት ሁለት ሃገራት እርምጃው ጠንከር ብሏል ከሚል ስጋት በድምፀ ተአቅቦ የወጡበትና 12 ሃገራት በሙሉ ድምፅ ያፀደቁት ማእቀብ በኤርትራ የሚመረተው ማእድን ትርምሱን ለማባባስ እንዳይጠቀምበት ኩባንያዎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ውል ያበጀ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።