የአፋር ክልል ህዝብ የኤርትራ ሰርጎ ገቦች በቱሪስቶች ላይ የፈጸሙትን ግድያ አወገዘ

አዲስ አበባ፤ ጥር 14 2004 /ዋኢማ/ – በአፋር ክልል የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን በመጎበኘት ላይ በነበሩ የዉጪ ዜጎች ላይ የኤርትራ መንግስት በላካቸዉ ሰርጎ ገቦች ሰሞኑን የተፈጸመዉን ጥቃት በማዉገዝ በሰመራ ከተማ  የተቃዉሞ ሰልፍ ተካሄደ ።

የኤርትራ መንግስት የላካቸዉ ሰርጎ ገቦች በክልሉ የኤርታሌን የመስህብ ሰፍራዎችን በመጎብኘት ላይ የነበሩ ሁለት የሃንጋሪ፣ ሁለት ጀርመንና አንድ የኦስትሪያ ዜጎች ሲገድሉ፣ ሁለቱ የሃንጋሪ ዜጎችን ደግሞ አቁስለዋል፡፡

እንዲሁም ሁለቱ ጀርመናዉያን ባልና ሚስቶችንና ሁለት ኢትዮጵያውያንን አግተው ወስደዋል።

ከክልሉ ከተለያዩ ዞኖች የተዉጣጡና በተቃዉሞ ሰልፉ ላይ የተሳተፉት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት የክልሉ ነዋሪዎች የኤርትራ መንግስት በላካቸዉ ሰርጎ ገቦች ቱሪስቶች ላይ የተፈጸመዉን ጥቃት አዉግዘዋል ።

በክልሉ የኤርታሌን የመስህብ ሰፍራዎች በመጎብኘት ላይ በነበሩ ቱሪስቶች ላይ የተፈፀመው የግድያ፣ የማቁሰልና የአፈና ወንጀል የኤርትራ መንግስት የክልሉን ልማት ለማደናቀፍ የያዘዉ እቅድ አካል እንደሆነም አስታውቀዋል ።

በኤርትራ መንግስት ሰርጎ ገቦች በተፈጸመዉ እኩይ ድርጊት ሳይዘናጉ በክልሉ የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ድሎች በመጠበቅ ቀጣይነት ያለውን ፈጣን ልማት በማረጋገጥ ድህነትን ለማሸነፍ ብርቱ ጥረት እንደሚያደርጉ ሰልፈኞቹ አረጋግጠዋል።

የአፋር ክልል ርዕስ መስተዳድር አቶ እስማኤል አሊሴሮ ባደረጉት ንግግር የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ሰላምና ልማት ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ሃይሎችን ከህዝብ በመነጠል በሁሉም ዘርፍ የተመዘገበውን ፈጣንና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ አስተዳደሩ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ።

በሰላማዊ ሰልፉ የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ አባላት የየከተሞቹ ነዋሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች ፣ተማሪዎችና የመከላከያና የፖሊስ ሰራዊት አባላት እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።።