ምክር ቤቱ ለገጠር መንገድ ፕሮግራም ትኩረት እንዲሰጥ አሳሰበ

አዲስ አበባ፤ ጥር 24 2004 /ዋኢማ/ – ወረዳን ከቀበሌ የሚያገናኘውን የገጠር መንገድ ፕሮግራም ላይ ትኩረት አድርጎ መንቀሳቀስ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

የምክር ቤቱ የአርብቶ አደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአርብቶ አደር አካባቢ የ2004 ዓ.ም. የግማሽ ዓመት የመንገድ ዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ፕሮግራሙን በተመለከተ የተዘጋጁ የሰነዶችን ዝግጅት ማጠናቀቅ፣ የተመረቱ መሣሪያዎችን ማጓጓዝና አነስተኛ ፕሮጀክቶችን በመለየት አማካሪዎችን ሥራ ማስጀመር በክልሎች ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብሏል፡፡

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንን ለክልሎች ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡

ፕሮግራሙን ለማስፈጸም የተጀመሩትን የመሣሪያዎች ምርት፣ የአቅርቦትና የሰው ኃይል ሥልጠና እሰከ ተግባር ፍፃሜ ድረስ በትኩረት መሥራት አለበት፡፡

በተለይ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች የገጠር መንገዶችን ለማከናወን ስትራተጂ መቀየስ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

የመንገድ ዘርፍ አሰራርን ለማሻሻልና የግንባታ ዋጋ ጥራትን ለመቆጣጠር የተነደፈው ስትራቴጂ መልካም መሆኑንም በግምገማው ላይ ተገልጿል፡፡

በመሆኑም ከተከናወነው ከስትራቴጂና ከዓላማ አንፃር ያስገኘውን ጠቀሜታ ለይቶ እንደምርጥ ተሞክሮ መጠቀም እንደሚያስፈልግም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

በተለይ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስና በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በሥርዓተ ፆታ የተከናወኑ ተግባራት በጥንካሬ የሚወሰዱ ሥራዎች መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡