የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በቁርጠኝነት ለመስራቅ ቃል ገቡ

አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2004/ዋኢማ/ – የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ያሉባቸውን ጉድለቶች በመገምገምና ምርጥ ተሞክሮዎቻቸውን በማስፋት ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ በመደራጀት በቁርጠኝነት ለመስራት ቃል መግባታቸው ተገለፀ። ለሁለት ቀናት በጠቅላይ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተካሄደው የኢትዮጵያ ሴት አመራሮች የጋራ ግምገማም ተጠናቋል።

የፌዴሬሽኑ አባላት ትናንት በተጠናቀቀው የሴት አመራሮች የጋራ አመታዊ የስራ ግምገማ ላይ ባወጡት የአቋም መግለጫ፤ ፌዴሬሽኑ በውስጥ ያሉ ማህበራትን ይበልጥ በማደራጀትና ያሉባቸውን ጉድለቶች በመገምገም በሚሊየን የሚቆጠሩ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱን በአቋም መግለጫቸው ገልጸዋል።

የፌዴሬሽኑ አባላት ባለ ስድስት የአቋም መግለጫ ያወጡ ሲሆን፤ በአቋም መግለጫቸው ላይም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የመንግስትና የባለድርሻ አካላት ከሚያወጧቸው አሰራሮች ጋር ለማቀናጀት መታሰቡም ተገልጿል።

እንዲሁም ሴቶች በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ይበልጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ ድህነትን ለማስወገድ ከማንኛውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት  እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ቀዳማዊ እመቤት አዜብ መስፍን በበኩላቸው፤ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሴቶች ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር ይገባቸዋል ብለዋል።

የብዙሃን ማህበራት ነፃ ሆነው በተጠናከረ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው። በቅድሚያ ማህበራቱ ያሉባቸውን ጠንካራና ደካማ ጎኖች መለየት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በሁለቱ ቀናት ግምገማም በየክልሎቹ ያሉ የፌዴሬሽኑ አባላት የተሰሩ ስራዎችን በማየት ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ለይቶ ማውጣት መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም በቀጣይ ለመስራት ለታቀዱ ስራዎች ግብዓት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ በ2004 የበጀት ዓመትም ፌዴሬሽኑ የብዙሃን ማህበራትን ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከተማ ድረስ በመውረድ ለማደራጀት መታቀዱን ገልፀዋል።

እንዲሁም ፌዴሬሽኑ በሁሉም ቀበሌዎች ደረጃውን ጠብቆ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

በ2003 የበጀት ዓመት በጥሩ እንቅስቃሴው በመምረጥ ለአባላቱ የቀረበው የትግራይ ምርጥ ተሞክሮም በጽሁፍና በሶፍት ኮፒ ለክልሎቹ እንዲደርስ መታቀዱንም ገልፀዋል።

መንግስት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተግባራዊ ያደረጋቸውን የተለያዩ የሴቶች ፓኬጆች ጋር በማያያዝ በርካታ የፌዴሬሽኑ ማህበራትን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ገልፀዋል።

በህንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ወይዘሮ ገነት ዘውዴና በጋና የኢትዮጵያ አምባሳደር ወይዘሮ ጊፍቲ አባስያ በበኩላቸው፤  በፌዴሬሽኑ የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማስኬድ በእውቀት ላይ የተመሰረተ እቅድ አቅዶ መስራት ይገባል ብለዋል።

በግምገማው ላይ ከተሳተፉት መካከል የአማራ፣ ቤንሻንጉል፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላና የአፋር  ክልል የፌዴሬሽኑ አባላትና አመራሮች በበኩላቸው፤ በጉባዔው ላይ በመሳተፋቸው በርካታ ተሞክሮዎችን ማግኘት መቻላቸውን መግለፃቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።