በጋሞጎፋ ዞን ቢታ ወረዳ ከመኸር እርሻ 712 ሺ ኩንታል የሚጠጋ ምርት ይሰበሰባል

አርባ ምንጭ፤ ታህሳስ 9/2004/ዋኢማ/ – በጋሞጎፋ ዞን ዲታ ወረዳ ከመኸር አዝመራ 712 ሺ ኩንታል የሚጠጋ ምርት ይሰበሰባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የወረዳው ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ቃይሴ ቃዲዳ ሰሞኑን ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል  እንደገለፁት፤ በመኸር አዝመራው ወቅት በ9ሺ 564 ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ፣ አተርና የጤፍ ዘር በመዝራት 711 ሺ 957 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ይገኛል ተብሎ ለሚጠበቀው ምርት አስፈላጊ የሆኑ የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ ለአርሶ አደሩ መከፋፈሉን ጠቁመው፤ ለዚህም ከ2ሺ ኩንታል በላይ ዩሪያ፣ ከ5ሺ ኩንታል በላይ ዳፕ፣ ከ9 መቶ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርጥ ዘርፍ፣ ከ2ሺ ኩንታል በላይ ድቡልቡል ድንች፣ ከ40 ኩንታል በላይ ጤፍና ባቄላ የምርጥ ዘር የተሰራጨቱን ገልፀዋል።

አቶ ጣይሴ አክለውም የግብርና ግብዓት አቅርቦቱ በወቅቱ መድረሱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው ተናግረዋል።

እንዲሁም ለአርሶ አደሩ የክህሎት ስልጠና የተሰጠ ሲሆን፤ በተጨማሪም የባለሙያ ድጋፍና ክትትል መካሄዱን ኃላፊው ተናግረዋል።

በወረዳው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተደረገው ጥረትም በአንዳንድ ቦታዎች በስንዴ ላይ የሚከሰተውን ዋግ ለመከላከልም በ56 ሄክታር መሬት ማሳ ላይ የመከላከል ስራ መስራት መቻሉን አስረድተዋል።

የመኸር ምርቱም ለመሰብሰብ መድረሱን ጠቁመዋል፤ በአካባቢው ያለውን ምህዳር ለመጠበቅ የተፋሰስ ስራ መሰራቱንም ኃላፊው ጨምረው መግለጻቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።