አዲስ አበባ, ታህሳስ 13 ቀን 2004 (ዋኢማ) – ለምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ ተቋማዊ መጠናከርና በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ኢትዮጵያ የምታከናውነው ተግባር ጉልህ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በቀጠናው የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረትም ኢትዮጵያ የጐላ ሚና እንዳላት ገልጧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በተለይ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በኢጋድ አባል አገራት ያለውን ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ ለማድረግ ኢትዮጵያ ቁልፍ ሚና በመጫወት ላይ ትገኛለች፡፡
በተለይ ሶማሊያ ውስጥ ያለውን ችግር በመፍታት፣ ለአገሪቱ የሽግግር መንግስት ድጋፍ በማድረግ፣ የአልሸባብን አቅም በማዳከምና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለሶማሊያ ችግር ትኩረት እንዲሰጥ ኢትዮጵያ ከኢጋድ ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደምትገኝ አረጋግጠዋል፡፡
እንዲሁም በአካባቢው ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠር ረገድ የሱዳን ሕዝበ ውሳኔ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት በምታደርገው ጥረት በኢጋድ አባል አገራት ዘንድ ከፍተኛ እምነት እንደተጣለባትም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ ኢጋድ በተባበሩት መንገስታት የታዛቢነት መቀመጫ ያገኘው ኢትዮጵያ ባደረገችው የዲፕሎማሲ ጥረት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢጋድን ተቋማዊ አቅም ለማጠናከር ኢትዮጵያ ከአባል አገራቱ ጋር በትብብር በመስራት ላይ እንደምትገኝም ጠቁመዋል፡፡
ክፍለ አህጉሩን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር በሚደረገው ጥረትም የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ2008 ጀምሮ የኢጋድ ሊቀመንበር በመሆን እየሰራች ትገኛለች፡፡ (ኢዜአ)