አበባ አምራች ሃብታሞች በገበያ ተወዳዳሪ የሚሆኑበት የአበባ ማምረቻ ማሠልጠኛ መመሪያ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ, ታህሳስ 14 ቀን 2004 (ዋኢማ) – በኢትዮጵያ አበባ አምራች ሃብታሞች የተሻለ ብቃት ኖሮአቸው በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚረዳ የአበባ ማምረቻ ማሠልጠኛ መመሪያ (ትሬኒንግ ማኑዋል) ተዘጋጀ፡፡

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለሥላሴ ተክኤ ከዘርፉ አምራች ኩባንያዎች ጋር በተዘጋጀው የሦስትዮሽ የጋራ የውይይት መድረክ ማጠናቀቂያ ላይ እንደተናገሩት መመሪያው በመድረኩ ፀድቋል፤ ከያዝነው ዓመት ጀምሮም ሥራ ላይ ይውላል ፡፡

ምርታማነት፣ ጥራትና በአነስተኛ ወጪ ማምረትን (ኩዊነር) የተመለከተው የመመሪያው ክፍል ደግሞ በቅርቡ በሚደረግ ሌላ ውይይት በሚሳተፉት አበባ አምራቾች፣ የሆርቲካልቸር አምራቾች ማህበር፣ የኢትዮ ኒዘርላንድ ፓርትነር ሺፕ፣ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ አየር መንገድ፣ ጉምሩክና ግብዓት አስመጪ ድርጅቶች በአጠቃላይ 48 በሚሆኑ ባለድርሻ አካላት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ በአበባ ልማት ላይ የተሰማሩ አምራቾች በተወዳዳሪነት አምርተው ገበያ እያገኙ በመሆኑ የእነርሱን አርአያ ለመከተልና በአገራችንም ዘርፉ እየተስፋፋ በመሆኑ ይህንኑ ለመደገፍ የተዘጋጀ የማሠልጠኛ መመሪያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

መመሪያው አበባ ተተክሎና አድጎ በተለይ ከተቆረጠ በኋላ ተጠቃሚው ዘንድ እስኪደርስ ከአራት ዲግሪሴንቲግሬድ ባልበለጠ ቅዝቃዜ ውስጥ የማቆየቱና ጥራትና ደረጃውን የመጠበቁ ሁኔታ ወሳኝ መሆኑን ያስገነዝባል።
በእጅ በሚያዝ (ሃንድ ቡክ) ደረጃ ጂኤልቪ በተባለ የኔዘርላንድስ አማካሪ ኩባንያና በኤጀንሲው ባለሙያዎች የተዘጋጀው ይኸው መመሪያ ኢትዮጵያ ለአበባ ምርት አመቺ መሆኗን የሚጠቁምና በዘርፉ ለሚሠማሩ ሃብታሞች በቂ መረጃ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
መመሪያው በየወቅቱ እየተሻሻለ የሚሄድ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡

አቶ ኃይለሥላሴ እንዳሉት የውጭ ምርጥ ተሞክሮን ባካተተና 38 የአበባ ኩባንያዎችን ባወያየ ሁኔታ መመሪያው የተዘጋጀው የአስር ወራት ፕሮጀክት በመቅረፅ ነው፡፡
መመሪያው በዘርፉ የተሰማሩ ሃብታሞች ምርታማነትን እንዲያሻሽሉ፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የተሻለ ጥራት እንዲኖራቸውና በአነስተኛ ወጪ ማምረት የሚችሉበትን አሠራር እንዲፈጥሩ ለማድረግ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በአበባ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች መመሪያው ወደፊት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚያስችላቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአበባ ምርትን ጨምሮ ከአትክልትና ፍራፍሬ ባለፉት አምስት ወራት ከ92 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ አግኝታለች። ከዚህ ውስጥ የአበባ ድርሻ 74 ነጥብ 5 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ነው። በዚህ በጀት ዓመት 401 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ኤጀንሲው እንዳለው።(ኢዜአ)