የመገናኛ ብዙሃንና የዜጎች የመረጃ ነጻነት አዋጅ ተግባራዊ ሆነ- የሕዝብ እንባ ጠባቂ

አዲስ አበባ, ታህሳስ 13 ቀን 2004 (ዋኢማ) – በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሁለት ዓመታት በፊት የጸደቀው የመገናኛ ብዙሃንና የዜጎች የመረጃ ነጻነት አዋጅ ተግባራዊ መሆኑን የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡

የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ልኡል ስዩም ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት አዋጁን ምክር ቤቱ ባጸደቀበት ወቅት ተግባራዊ የማስፈጸሚያ አስፈላጊ ዝግጅት ለማድረግ የሁለት ዓመት ጊዜ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

በዚሁ መሰረት ተቋሙ ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር ልዩ ልዩ ሰነዶችንና ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ባሉ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል አደራጅቶ የማቋቋም ስራ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አንድ ግብረ ሐይል ተቋቁሞ የመረጃ መብት የቅሬታ ማስተናገጃ የአፈጻጸም መመሪያና መረጃ የማግኘት መብት ድንጋጌዎች /የማይገለጹ መረጃዎች አጭር ማብራሪያ/ እና ሌሎች ሰነዶች መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል፡፡

የመንግስት አካላትና የሕዝብ ግንኙነቶች ዜጎች የሚፈልጓቸውን ማናቸውንም መረጃዎችና የተቋማቱን አሰራር የሚገልጹ ሪፖርቶች በማዘጋጀት በአዋጁ ድንጋጌ መሰረት አትመው ማድረስ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
በተቋማቱ የመረጃ አያያዝ ስርዓት መጠናከር እንዳለብት የገለጹት ዳይሬክተሩ አዋጁ ወደ ትግበራ ሲገባም በተወሰነ ደረጃ የሚያጋጥሙ ድክመቶች ቢኖሩ እየተስተካከሉ ይሄዳሉ ብለዋል፡፡

አገራዊ የጋራ አመለካከትና ዴሞክራሲያዊነት ለመፍጠር የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻናት አዋጅ በተግባር መፈተሽ እንዳለበት በመንግስት አካለት ግልጽ አሰራርና ትክክለኛነትን ለማስፈን አዋጁ በየደረጃው ባሉ ተቋማት ሁሉ ዘንድሮ ተግባራዊ መደረግ ይጠበቅበታል ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የአቅም ግንባታ ስራም በየደረጃው ለመስራት ተቋሙ ሰፊ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመው በዚህ ረገድ ያሉትን የግንዛቤ ክፍተቶች ለመሙላት ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሚስጥራዊነት የቆየ ባህል መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ይህንን ኋላ ቀር አመለካከት በመስበር ዜጎችና መገናኛ ብዙሃን የሚፈልጓቸውን መረጃዎች የመስጠት ስራ ለመልካም አስተዳደርና ልማት በእጅጉ የሚያግዙ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተፈላጊውን መረጃ ለዜጎች ለማድረስ የመንግስት ቁርጠኝነት መኖሩን ገልጸው አዋጁን የማስፈጸም ሰፊ ስራም እስካሁን ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም ከብሔሪዊ ቤተ መዛግብትና በተ መጸሐፍት ጋር በመተባበር አገራዊ የሰነድ ዝግጅት ፖሊሲ መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል፡፡

የመረጃ ነጻነት አዋጅ 590/2000 በህዳር 25 ቀን 2001 ዓ/ም በነጋሪት ጋዜጣ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ በአዋጁ ክፍል 3 ድንጋጌዎች ተፈጻሚ የሚሆኑትም የዝግጅት ጊዜው ካበቃ በኋላ እንደሚሆን ይገልጻል፡፡
ተቋሙ ምክር ቤቱን ተጨማሪ የአንድ አመት የዝግጅት ጊዜ ጠይቆ የተራዘመለት መሆኑን አስታውሰው ምክር ቤቱ የአዋጁ ትግበራ ያለምንም ተጨማሪ ጊዜ አሁኑኑ እንዲጀምር ወስኗል ብለዋል፡፡ (ኢዜአ)