ደቡብ ኮሪያ ውጤታማ የልማት ልምዷን ለኢትዮጵያ ለማጋራት ከፍተኛ ፍላጎት አላት

አዲስ አበባ, ታህሳስ 18 ቀን 2004 (ዋልታ) – ደቡብ ኮሪያ በልማት ረገድ ያካበተችውን ተግባራዊ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማጋራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ገለጹ።

አምባሳደር ጆንግ ጊዩን ኪም ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ ለአገራቸው ነፃነትና ሰላም መከበር የከፈለችውን መስዋዕትነት በመዘከር ለልማቷ የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማድረግ ለማድረግ ቁርጠኛ ናት።
አገራቸው በጤና፣በትምህርት፣በግብርናና በአቅም ግንባታ ዘርፎች ትብብር በማድረግ ላይ መሆኗንም አስረድተዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ መጠን ለማሳደግ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሚገኝም አምባሳደር ኪም አመልክተው፣ በዚህም ነጻ የንግድ ቀጣና ለመመስረትም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።ቀደም ሲልም በኢትዮጵያ የንግድ ማዕከል መቋቋሙን አስታውሰዋል።

በአገሮቹ መካከል ያለው የትብብር ግንኙነት አገራቸው ወደ ኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ በበለጠ ለማጠናከር እንደሚያስችላትም ገልጸዋል።

በሁለቱ አገሮች ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል በየጊዜው እየተደረገ ያለው ጉብኝት ፍሬያማ እንደሆነ ገልጸው፣በዚህም በበርካታ መስኮች ትብብሩ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በአገሮቹ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መከፈቱንም አምባሳደር ኪም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካን ጉዳዮች በማራመድ እየተጫወተች ያለችው ሚና አገራቸው አድናቆት እንዳላት አምባሳደር ኪም አስታውቀዋል።

አገሪቱ የፖለቲካዊ መረጋጋትና የማህበረ- ኢኮኖሚ ልማት ለማምጣት የምታደርገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አመልክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋምና አረንጓዴ ልማትን በመፍጠር ግንባር ቀደም አገር በአፍሪካ አህጉር እየተጫወተች ያለው ድርሻም በአገራቸው እንደሚደነቅም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገራቸው ኤዥያን ኤርዌይስ አባል በሆነበት ስታር አሊያንስ አባል መሆኑ የአገሮቹን ግንኙነት ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አምባሳደር ኪም አመልክተዋል። (ኢዜአ)