ኢትዮጵያ የልማት ግቧን ለማሳካት ርብርብ እያደረገች እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18፣ 2004 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረኮች የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ስትራቴጂዋን በማስረፅ የልማት ግቧን ለማሳካት ርብርብ እያደረገች እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ተናገሩ።

አቶ ሃይለማሪያም ዛሬ የመስሪያ ቤታቸውን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

በዚሁ ወቅት እንዳሉት ሀገሪቱ የኢንቨስትመንትና የንግድ ማዕከል እየሆነች መጥታለች።

ባለፉት ስድስት ወራት 186 የውጭ ባለሃብቶች ከ197 በሚበልጡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ለመሰመራት ፍቃድ የወሰዱበት ሂደት ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ የተሰራውን ስራ ያሳያልም ብለዋል።
የውጭ ዕርዳታና ብድርን አሰባስቦ የልማት ግቡን ከግብ ለማድረስም የተለያዩ ስራዎች እንደተሰሩ ገልጸዋል።

በዚህም ከቻይና፤ አሜሪካ፤ ሳውዲ አረቢያ መንግስታት እንዲሁም የአፍሪካና ዓለም ባንክን ከመሳሉ ተቋማት አንድ ቢሊየን ዶላር ዕርዳታና ብድር ማግኘት እንደተቻለ ጠቅሰዋል።

ቀጠናውን በማተራመስ በኢትዮጵያ ላይ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም በሚንቀሳቀሰው የኤርትራ መንግስት ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል የተደረገው እንቅስቃሴም ውጤታማ እንደሆነ መናገራቸውን ፋና ዘግቧል።