የ2003 – 2004 ዓ.ም የመኽር ምርት ይገኛል ተብሎ ከታቀደው የ15 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18፣ 2004 (ዋልታ)- የ2003 – 2004 ዓ.ም የመኽር ምርት ይገኛል ተብሎ ከታቀደው የ15 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በመሰረታዊ የእድገት አማራጭ በ2003 – 2004 ዓ.ም የመኽር እርሻ ይገኛል ተብሎ የታቀደው የግብርና ምርት ከእቅዱ የ15 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ አለው።

በቅድመ ትንበያ መረጃዎች መሰረት ይገኛል ተብሎ የተገመተው የግብርና ምርት መጠን 218 ሚሊየን ኩንታል መሆኑን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ተናግረዋል።

ከዚህም በመነሳት የተገኘውን ውጤት በጣም ጥሩ ሲሉ ይገልጹታል ሚኒስትሩ።

ስለ መኽር እርሻው አስተያየታቸውን የገለጹት ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን መቂ ወረዳ እና ከአማራ ክልል አዊ ዞን ዳንግላ ወረዳ አርሶ አደሮች ከዓምናው የመኽር ወቅት የተሻለ ምርት አግኝተናል ብለዋል።

ለገበያ የሚቀርበው የግብርና ምርት በሚፈለገው ደረጃ አለማደግ የዋጋ ንረትን ከሚያስከትሉ ምክንያቶች አንዱ ነው የሚሉት አቶ ተፈራ ለችግሩ በመሰረታዊ መፍትሄነት የግብርና ምርትን ማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑን አንስተዋል።

ዘንድሮ ከእቅድ በላይ ምርት መገኘቱም በገበያው ላይ ለሚስተዋለው የግብርና ምርት ዋጋ ንረት መቀነስ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል። ለዚህም ከወዲሁ መልክቶች እየታዩ መሆኑን ያነሳሉ።

በቀጣይም ወደ ገበያው የሚገባው ምርት ትርጉም ባለው መልኩ አርሶ አደሩን እንዲጠቅምና ገበያውን እንዲያረጋጋ የገበያ ሰንሰለቱን ማሳጠር ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትና ክህሎት ማሳደግ፤ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦትን ከፍ ማድረግ የአርሶ አደሩን የማምረት አቅም ለመገንባት ብሎም በምርት ዘመኑ ለማግኘት የታቀደውን ውጤት ለማሳካት ከተከናወኑ ተግባር መካከል መሆናቸውን ፋና ዘግቧል።