በፍራንክፈርትና በአካባቢዋ በረቂቅ የዲያስፖራ ፖሊሲ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19 2004 /ዋኢማ/ – በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በረቂቅ የዲያስፖራ ፖሊሲ ላይ መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በከተማዋ በሚገኘው የቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ከኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ጋር በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል።

የሚኒስቴሩ የዲያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወልዴ ባደረጉት ገለጻ ረቂቅ ፖሊሲው በዋነኛነት በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጥቅም ለማስከበርና ከአገራቸው ጋር የጠበቀ ትስስር እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ግቦች እንዳሉት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያውያኑንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑን  ትክክለኛ መረጃ መያዝ፣የዲያስፖራ ተቋማትን ማጠናከር፣ኔትወርክና የራሱ ድረ ገጽ እንዲኖረው ማድረግ የፖሊሲዉ ግቦች መሆናቸዉንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

እንዲሁም የአገርህን እወቅ ፕሮግራም በማዘጋጀት በተለይ አዲሱ ትውልድ ከአገሩ አንዳይርቅና የአገሩን ባሀል ይዞ የሚያስቀጥሉት የማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች እንዳሉትም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች በበኩላቸው አገርንና ፖለቲካን ለያይቶ ያለማስቀመጥ ችግር እንደሚታይ ገልጸው፣አገራዊ ጉዳዮችን ከፓርቲ ጥቅም ለይቶ በማየት በፖሊሲው ላይ ተመስርቶ ለሚወጣው ዓዋጅ ተግባራዊነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።