ባለፉት አምስት ወራት መንግስት ለመሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19 2004 /ዋኢማ /– በያዝነው የበጀት ዓመት አምስት ወራት መንግስት ለመሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ከሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ብር በላይ ድጎማ ማድረጉን የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የንግድ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሲራጅ አሊ እንደገለፁት በስኳር፣ በፓልም ዘይትና ስንዴ ላይ እየተደረገ ያለው ከፍተኛ መጠን ያለው የድጎማ ወጪ  ምርቶቹ በገበያ ላይ የዋጋ መረጋጋት እንዲያመጡ አስችሏል።

በመሰረታዊ ፍጆታዎች ላይ በተፈጠረው የገበያ ጉድለት ምክንያት የህብረተሰቡን አኗኗርና ህይወት የሚፈታተኑ ናቸው ተብለው የተለዩ ምርቶችን አሁንም ድረስ መንግስት  በመደጎም ላይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዉ  የስኳር፣ ስንዴና ዘይት ምርቶች ላይ እየተደረገ ያለው ድጎማ በሸቀጦቹ ላይ ታይቶ የነበረውን  ከፍተኛ የዋጋ ንረት ማረጋጋቱን ተናግረዋል።

ከሃምሌ ወር ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር አጋማሽ ድረስ ለፓልም ዘይት የተደረገው ድጎማ 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ሲሆን ለስኳር ከ932 ሚሊየን ብር በላይ ተደጉሟል።

እንዲሁም ለሰንዴ ምርት ከ204 ሚሊየን ብር በላይ በመደጎም ምርቶቹን ከውጭ በማስመጣት ለህብረተሰቡ በፍትሃዊነት በሽያጭ ማቅረብ ተችሏል።
የስንዴን ምርት ለህብረተሰቡ በየሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ማቅረብ ከተጀመረ ከአንድ ወራት ወዲህም በገበያ ላይ ምርቱ ከ60 እስከ 70 ብር ቅናሽ ማሳየቱን ሚኒስትር ዴኤታዉ

ተናግረዋል።
ከተመረጡ የዱቄት ፋብሪካዎች ዱቄት ወስደው ዳቦ የሚያመርቱ ዳቦ ቤቶችንም የመቆጣጠሩ ስራ እንዲሁ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ባለ መቶ፣ ሁለት እና ሦስት መቶ ግራም መጠን ያለውን ዳቦ ለተጠቃሚዎች በተወሰነው መጠን መሰረት እንዲያቀርቡም እየተደረገ ነው።

ተጠቃሚው ህብረተሰብ በምርቱ ላይ የመጠን መቀነስ ካጋጠመው በአቅራቢያው ለሚገኝ የፍትህ አካል ወዲያው በማሳወቅ አስፈላጊውን እርምጃ ማስወሰድ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ከ70 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ የዘይት ምርት ወደ ሃገር ውስጥ መግባቱን የተናገሩት አቶ ሲራጅ በአሁኑ ሰዓትም በተለያዩ መጋዝኖች ከ32 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ዘይት እንደሚገኝ እና ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ከሚገኙ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በጋራም ሆነ በተናጠል መግዛት እንደሚችል ገልጸዋል።

የስኳር ምርትም እንዲሁ በሃገር ውስጥ እየጨመረ ካለው የምርት አቅርቦት ጋር ተዳምሮ መንግስት ከውጭ የሚያስመጣው ስኳር በሃገር አቀፍ ደረጃ መረጋጋት መፍጠሩንም ተናግረዋል።

ኢኮኖሚው በድጎማ እንዲመራ መንግስት ፍላጎት የለውም ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው ዋናው መፍትሄ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን ክፍተት ለይቶ የማጥበብ ስራን ማከናወንና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ነዉ ማለታቸዉን የዘገበዉ ፋና ነዉ።