በደቡብ ክልል በግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ተካሄደ

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 19 2004 /ዋኢማ/- በደቡብ ክልል በ 560 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ማከናወኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ብርሃኑ ጦፋ  እንዳስታወቁት ከባለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ  በክልሉ ለከፍተኛ የመሬት መራቆት በተጋለጡ 90 ወረዳዎች በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ወስጥ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ተከናዉነዋል፡፡

ከተከናወኑት ሥራዎች መካከል 77 ሺህ ኪሎ ሜትር የእርከን፣ 56 ሺህ ሄክታር የተጎዳ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ የመከለል፣ 32 ሺህ ኪሎ ሜትር የክትር ሥራ፣ሰባት ሺህ ኪሎ ሜትር የጎርፍ መቀልበሻ 16 ሺህ ሜትር ኩብ የጋቢዮን እና 28 ሺህ ሜትር ኩብ የግማሽ ጨረቃ እርከን ሥራዎች እንደሚገኙበት ዋና የሥራ ሂደት ባለቤቱ አመልክተዋል፡፡

በተፋሰስ ልማቱ የቴክኒክ እና የተደራሽነት ችግሮችን ለመፍታት ለ 11 ሺህ የልማት ጣቢያ ሠራተኞች እና ለ143 ሺህ ቀያሽ አርሶአደሮች በተግባርና በንድፈ ሀሳብ ላይ ያተኮረ የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ ሥልጠና መሰጠቱን አስረድተዋል ፡፡

በተፋሰስ ልማት ተጨባጭ ለውጥ ካመጣው ከትግራይ ክልል ልምድ በመውሰድና ከደቡብ ክልል ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በመከለስ በክልሉ የተፋሰስ ዕቅድ ውስጥ እንዲካተት መደረጉንም አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል ፡፡
የክልሉ መንግስት ተፋሰስን መሠረት ያደረጉ የአፈርና ውሃ ሥራዎች @ የሰብልና የእንሰሳት ሀብት ልማቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ ነድፎ በሥራ ላይ ማዋሉንም አስረድተዋል፡፡