የአገር ገጽታ ግንባታ ሥራን በተቀናጀ መልኩ የሚሰራ የምክክር መድረክ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 20 2004 /ዋኢማ/ – የአገር ገጽታ ግንባታ ሥራን በተቀናጀ መልኩ ለመሥራት የሚያስችል የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ የምክክር መድረክ  መመሥረቱን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ትናንት እንዳስታወቀው የምክክር መድረኩ የኃይማኖት ተቋማትን፣ የንግድ ምክር ቤቶችን፣ ከፍተኛ የግል ትምህርት ተቋማትንና የምርምር ተቋማትን በአባልነት ያቀፈ ነው፡፡

በሚኒስቴሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ጌታቸው ረዳ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዳራሽ በተካሄደ የምስረታ ስብሰባ ላይ ባሰሙት ንግግር የገጽታ ግንባታ ሥራ የሕዝብ ለሕዝብ ሥራ እንደመሆኑ መጠን በተጠናከረ መልኩ ለመሥራት የባለድርሻ አካላት የማይተካ ሚና አላቸው፡፡

የምክክር መድረኩ መመስረት የተሳካ የገጽታ ግንባታ ሥራ ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ዳይሬከተሩ ገልጸዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የአገር ውስጥ የሚዲያ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ንጉሴ በበኩላቸው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተናጠል የሚያደርጉት የገጽታ ግንባታ ሥራ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ለማካሄድ መድረኩ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በምክክር መድረኩ የተካተቱ ባለድርሻ አካላት በዚህ ወሳኝ አገራዊ የገጽታ ግንባታ ሥራ በተቀናጀ ሁኔታ ለመስራት መካተታቸው እንዳስደሰታቻው ገልጸው ለስኬቱ ጠንክረው እንደሚሰሩ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡