በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የሦስት ሆስፒታሎች ግንባታና የማስፋፋት ሥራ ተጀምሯል

ሐረር፤ ታህሳስ 21 2004 /ዋኢማ/ – በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት የዞኑን ነዋሪዎች የጤና አገልግሎት ለማሳደግ የሦስት ተጨማሪ ሆስፒታሎች ግንባታና የማስፋፋት ሥራ መጀመሩን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የሆስፒታሎቹ ግንባታና የማስፋፊያ ሥራ የሚከናወነዉ ከ79 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ነዉ።

የዞኑ ጤና መምሪያ  ኃላፊ አቶ አሊ አብዱላሂ እንደገለጹት በዞኑ የሁለት አዳዲስ ሆስፒታሎችና የአንድ ሆስፒታል የማስፋፊያ ሥራ ሰሞኑን ተጀምሯል፡፡

የሁለቱ አዳዲስ ሆስፒታሎች ግንባታ በዞኑ ጨለንቆና በደኖ ከተሞች የሚከናወን ሲሆን የደደር ሆስፒታል የማስፋፊያ ሥራም በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አቶ አሊ ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የሚገነቡት ዘመናዊ ሆስፒታሎች የተሟላ የህሙማን መኝታ ክፍሎች፣የቀዶ ጥገና፣የተመላላሽ፣የራጅ፣ የላቦራቶሪ፣የምርመራ፣የመድሀኒትና ሌሎችንም የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች አካተው የሚከናወኑ ናቸዉ፡፡

ሆስፒታሎቹ በተያዘላቸው የጊዜ ሠሌዳ ተጠናቀዉ ለአገልግሎት ሲበቁ  ከ750 ሺህ ለሚበልጡ የሜታ፣የበደኖና ደደር ወረዳዎችና ለሌሎች የአጎራባች ወረዳ ነዋሪዎች የተሟላ የህክምና አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳላቸው ኃላፊዉ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በዞኑ ሦስት ብቻ የነበረውን የሆስፒታሎች ቁጥር ወደ ስድስት በማሳደግ ለዞኑ ነዋሪዎች የተሻለና ዘመናዊ የህከምና አገልግሎት ለመስጠት እንደሚቻል አቶ አሊ ገልፀዋል።