የአዲስ አበባ ከተማ 125ኛ ዓመት በዓል የታዩ ለውጦችና ቀጣይ ሥራዎችን በሚያሳይ መልኩ ይከበራል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21 2004 /ዋኢማ/ – የአዲስ አበባ ከተማ 125ኛ ዓመት የልደት በዓል አከባበር ባለፉት ዓመታት የታዩ ለውጦችና ወደፊትስ ምን መከናወን እንደሚገባ ሊያሳይ በሚችል መልኩ መከበር እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አባተ ስጦታው የበዓሉ አከባበር መሪ እቅድ ላይ ከአቢይ ኮሚቴዎች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ እንደተናገሩት በዓሉን ማክበር ብቻ ሳይሆን የታዩትን ለውጦች ማስገንዘብ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በመዲናዋ በኢንቨስትመንት፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በባህልና በመሳሰሉት የታዩትን ለውጦችን በማሳየት የሕዝብ በዓል ሆኖ መከበር እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

በየደረጃው ሰፊ ንቅናቄ በመፍጠር ከእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ጋር ትርጉም ያለው በዓል ለማክበር ዓቢይና ንዑሳን ኮሚቴ በመሠየም መሪ እቅድ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴውም በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ለማክበር የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባ አሳስበው በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበርም ጠቁመዋል፡፡

በዓሉ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ግንዛቤ የሚፈጠርበት እንደሚሆንና መላው የከተማው ነዋሪዎች ለከተማው እድገት የሚነሳሰበትን ሁኔታ በሚፈጥር መልኩ መከበር  እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡

በአስተዳደሩ የአገር ውስጥና የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት አማካሪ አቶ ከፍያለው አዘዘ መሪ እቅዱን ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት የበዓሉ አከባበር የአገሪቷን ብሎም የከተማዋን አዎንታዊ ለዉጦች በማጠናከር ለበለጠ ውጤት ህዝቡን በማነሳሳት ይከበራል፡፡

እንዲሁም የከተማዋን ቀደምት ታሪኮች በማስታወስ ትክክለኛውንና በመጪው ትውልድ ሊወሰድ የሚገባውን በማስገንዘብ ዘንድሮ 125ኛው ዓመት ክብረ በዓልን በፈጣን የእድገት መስመር ላይ ሆና ለማክበር ዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ መሪ እቅዱን የሚያጠናክሩ አስተያየቶች መጠቆማቸውንና አስተዳደሩም አስተያየቶቹን በገብአትነት መቀበሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡