በደቡብ ክልል የጤና መድህን ዋስትና ሥርዓት ተግባራዊ በመሆን ላይ ነው

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 21 2004 /ዋኢማ/– በደቡብ ክልል የጤና መድህን ዋስትናን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ ::

በቢሮው  የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ያለው አባተ  እንዳስታወቁት የጤና መድን ዋስትና ሥርዓቱ እየተካሄደ የሚገኘው በክልሉ ለሙከራ በተመረጡ በይርጋዓለም ከተማ፣ በደንቦያና በዳሞት ወይዴ ወረዳዎች ነው ::

የጤና መድህን ዋስትናን ተግባራዊ ለማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሙከራ ከተመረጡት 12 ወረዳዎችና ከተሞች መካከል ሦስቱ በደቡብ ክልል የሚገኙ መሆናቸውን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዉ ገልጸዋል::

የጤና መድህን ዋስትና ለሙከራ በተመረጡት ሁለቱ ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደር ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ውስጥ ለሚገኙ ሠራተኞች  በዋስትናው ጠቀሜታ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተዘጋጅተዋል::

የሙከራ ሥራው ከተጀመረ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 12 ሺህ 339 ሠራተኞች የጤና መድህን ዋስትና ግº ለመፈጸም መቻላቸውን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ገልጸዋል::

የጤና የመድህን ዋስትናውን ከገዙት ሠራተኞች መካከል የጤና መታወክ ያጋጠማቸው 1ሺህ 504 ሠራተኞች እና የቤተሰብ አባሎቻቸው በገቡት የመድህን ዋስትና መሠረት ተጨማሪ ክፍያ ሳያስፈልጋቸው ከመለስተኛ እስከ ከፍተኛ የሚደርስ የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን አስረድተዋል::

ቢሮው በተያዘው የበጀት ዓመት በክልሉ በተመረጡ አካባቢዎች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ በመሆን ላይ የሚገኘውን የጤና መድህን ዋስትና አፈጻጸም እንደሚገመግም ጠቁመዋል::

በቀጣይ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የተገኙ የሙከራ ውጤቶችን በመቀመር የጤና     መድህን ዋስትና ሥርዓት በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ አመልክተዋል::