በደቡብ ክልል የግሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ የዜጎችን የሥራ አጥነት ችግር እየፈታ ነው

ሀዋሳ ፤ ታህሳስ 24 2004 /ዋኢማ/ – በደቡብ ክልል የግሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ የዜጎችን የሥራ እጥነት ችግር እየፈታ መሆኑን የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው በክልሉ በመስፋፋት ላይ የሚገኘው የግሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ የእርሻና የኢንዱስትሪ ምርት አቅርቦትን ከማሳደጉ  በተጨማሪ በክልሉ የሥራ ዕድል አማራጮችን በማስፋት ላይ ይገኛል።

በክልሉ የግሉን የኢኮኖሚ ዘርፉ ለማጠናከር የኢንቨስትመንት አዋጅ ተግባራዊ ከሆነበት ከ 1985 ዓ.ም ወዲህ 108 ሺህ 503 ዜጎች የቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን መቻላቸውን በቢሮው የመንግሥት ኮሚኒኬሽን  ደጋፊ የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ አበበ ዲንጋሞ ገልጸዋል።

የግሉ የኢኮኖሚ ዘርፍ በፈጠረው የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ከሆኑት የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከ78 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወጣቶችና ሴቶች መሆናቸውን ቢሮው ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጡን የሥራ ሂደት ባለቤቱ አስረድተዋል።

በክልሉ የሥራ አማራጮች ሊፈጠሩ የቻሉት 57 ቢሊዮን 643 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያዝመዘገቡ 5 ሺህ 803 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በመደረጋቸው መሆኑን አቶ አበበ  ተናግረዋል።

የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቹ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ ፣በኮንስትራክሽን ፣በሪል ስቴት፣ በአበባ ምርት እና ፍራፍሬ፣ በሆቴል እና  በተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ዘርፎች የተሰመሩ ባለሀብቶች መሆናቸውን የሥራ ሂደት ባለቤቱ አብራርተዋል።

በክልሉ ቀደምሲል የምርት ተግባር ከጀመሩት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከ 2  ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 305 ፕሮጀክቶች በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ቢሮው የመሬት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ለኢንቨስትመንት የሚውሉ የከተማና የገጠር መሬቶችን ለመለየት የሚያስችል ዘመናዊ የመሬት የመረጃ ሥርዓት  መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በክልሉ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስጠናት 765 አማራጭ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ሀሳቦችን በህትመት እና በቢሮው ድረ ገጽ አማካኝነት ለተጠቃሚ ባለሃብቶች ማቅረቡን አቶ አበበ ተናግረዋል።