በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የገጠር ማዕከላትን ከወረዳ ከተሞች የሚያገናኙ መንገዶች ግንባታ ተጀመረ

ሐረር፤ ታህሳስ 24 2004 /ዋኢማ/ –   በምስራቅ ሐረርጌ ዞን   የገጠር ማዕከላትን ከወረዳ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ የ786 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታና ደረጃ የማሳደግ ሥራ ተጀመረ።

የዞኑ መንገዶች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው ግንባታዎቹ የሚከናወኑት ከ305 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ነው፡፡

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን መንገዶች ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲራጅ ኢብሮ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት በዞኑ ሰሞኑን የተጀመሩት የመንገድ ግንባታ ሥራዎች 19 የወረዳ ከተሞችን ከቀበሌ የልማት ማዕከላት ጋር እርስ በርስ የሚያገናኙ ናቸው፡፡

በታህሳስ ወር አጋማሽ ከተጀመሩት 786 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገዶች ግንባታ መካከል 765 ኪሎ ሜትሩ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 21 ኪሎ ሜትሮች ደረጃቸው ተሻሽለው የሚሰሩ መሆናቸውን አቶ ሲራጅ ተናግረዋል፡፡

የመንገዶቹ ግንባታ በ36 ሀገር በቀል የስራ ተቋራጮችና በ10 አማካሪ ድርጅቶች አማካኝነት የሚካሄዱ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው የመንገድ ሥራዎቹ በዓመቱ መጨረሻ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ የየወረዳዎቹ አርሶአደሮች ምርቶቻቸውን በቀላሉ ለገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በዞኑ 782 ኪሎ ሜትር የደረሰውን ጠቅላላ የዋና ዋና መጋቢ መንገዶች ርዝመት ወደ 1ሺህ537 ኪሎ ሜትር በማሳደግ የዞኑን የገጠር መንገድ ሽፋን   እንደሚያሻሽለው አብራርተዋል፡፡

በዞኑ በዓመቱ ለሚካሄደው የመንገድ ግንባታና ደረጃ የማሳደግ ሥራ ከተመደበው 305 ሚሊዮን ብር ውስጥ 50 በመቶው በክልሉ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው 50 በመቶ ያህሉ ደግሞ በወረዳ መስተዳድሮችና በህዝቡ እንደሚሸፈን አስታውቀዋል፡፡