የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለመሳካት የሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ

ጋምቤላ፤ ታህሳስ 25 2004 /ዋኢማ/ – የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለመሳካት የሴቶችና የወጣቶች ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ የሴቶችና የወጣቶች አደረጃጀቶችን ተቋማዊ ብቃት ለማጎልበትና ከመንግስት ፈፃሚ አካላት ጋር የሚኖራቸውን ትብብር ለማጠናከር  ያለመ የምክክር መድረክ ሰሞኑን በጋምቤላ ተካሂዷል።

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ በምክክር መድረኩ ላይ እንደተናገሩት የአምስት ዓመቱን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመሳካት የሴቶችና የወጣቶች ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ ነው።

የሴቶችና የወጣቶች አደረጃጀቶች መንግስት ያወጣቸውን ፖሊሲዎችና ዕቅዶች በመተግበር መላውን ህብረተሰብ ከመጥቀማቸው በተጨማሪ የሴቶችንና የወጣቶችን  መብትና ጥቅም ለማስከበር ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ወይዘሮ ዘነቡ ተናግረዋል፡፡

የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች በአብዛኛው የአባላቶቻቸውን መብትና ጥቅም ከማስከበር ይልቅ የሌላ ወገን መጠቀሚያ መሳሪያ በመሆን እና  የግል ጥቅም በማሳደድ ላይ የተጠመዱ መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትሯ በተለይም አመራር አካላቱ የሴቶችንና የወጣቶችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ  ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡቦንግ በበኩላቸው መንግስት በቀረፃቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች መሰረት የሴቶች ፣የህፃናት የወጣቶች የልማት ተሳትፎና ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ማብራሪያ የኢፌዲሪ የወጣቶች ፖሊሲ  በክልሉ የሚገኙ ወጣቶችን የልማት ተጠቃሚ እያደረገ ነው።ሕፃናትም የህፃናት ፓርላማ በማቋቋም ህገ መንግስቱን ተገንዝበው ለመብታቸው ከወዲሁ እንዲታገሉ ለማስገንዘብ ጥረት እየተደረገ ነው።የሴቶችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለማረጋገጥም በክልሉ የቤተሰብ ሕግ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ለሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች  ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ ከማስቻሉም በላይ በልማት፣በመልካም አስተዳደር እና በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ እንዲሁም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን በመተግበር  ያላቸውን ተሳትፎ  ያጠናክራል ብለዋል አቶ ኡሞድ  ።

በምክክር መድረኩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል፣የጠቅላይ ሚኒስትር የህዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ የሁለቱም ክልሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት መሳተፋቸውን ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘግቧል፡፡