አዲስ የወጣው የመሬት ሊዝ አዋጅ ሁሉንም ሕብረተሰብ ተጠቃሚ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26 2004/ዋኢማ/– አዲስ የወጣው የመሬት ሊዝ አዋጅ በየደረጃው ሁሉንም ሕብረተሰብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የአስተዳደሩ ዋና ሰራ አስኪያጅ አቶ ኃይሌ ፍስሐ ዛሬ ከመዲናዋ ሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች ጋር በተወያዩበት ወቅት እንዳሉት አዋጁ ሁሉም የከተማዋ ነዋሪ የመንግስትና የሕዝብ ሃብት የሆነውን መሬት በአግባቡ እንዲጠቀም ያደርጋል፡፡

የመሬት አዋጁ በከተማ ኢንዲስትሪን ለማስፋፋትና ነዋሪውን ተጠቃሚ ለማድረግ በገጠር ደግሞ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግና በሁሉም አካባቢዎች መሰረተ ልማትን በአግባቡና ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለማስፋፋት ያግዛል ብለዋል፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት በከተማ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል እየፈጠሩ ላሉት የአነስተኛና ጥቃቅን የስራ ዘርፎች መሬት ለማቅረብ የሚረዳ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ የመሬት ፖሊሲው የኢኮኖሚና ማሕበራዊ አድገትን በማፋጠንና የከተማውን ሕዝብ ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ የበኩሉን አስተዋጾ እንደሚያበረክት አስረድተዋል፡፡

ፖሊሲው በከተሞች መሬትን በማከፋፈል ረገድ ፍትሐዊነትን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ ይህንን በአግባቡና በትክክለኛ መንገድ ለማስፈጸም የሚያችል መሆኑንም የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

የከተማ መሬት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከከተሞች እድገት ፍጠነት አኳያ እጥረት የሚታይበትና በአንዳንድ አካላት ባለቤት እንደሌለው ተቆጥሮ በሕገወጥ መንገድ ሲባክን እንደነበርም ገልፀዋል፡፡

ከዚሁ ጎን ለጎንም ከመንግስት የወሰዱትን መሬት አልምቶ ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ ምንም አይነት እሴት ሳይጨምሩ አየር ባየር ወደ ሶስተኛ ወገን በማሸጋገር ባልለፉበትና ባልደከሙበት የጥቂቶች መክበሪያ ሲሆን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ባጠቃላይ በመላ አገሪቱም ሆነ በከተማዋ ከመሬት ልማቱ የተገኘውን ጥቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና መንግስትና ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲቻል ሁሉም ለአዋጁ ተፈጻሚነት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ (ኢዜአ)