ትምህርት ሚኒስቴር ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26 2004/ዋኢማ/– በአገሪቱ እየተካሄደ ላለው የልማት ፕሮግራም መሳካት ትምህርት ሚኒስቴር ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ዛሬ በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ከተሰማሩ ባለሀብቶች ጋር በተደረገ የምክክር መድረክ እንዳሉት ትምህርት ለአገሪቱ የልማት ፕሮግራሞች ሁሉ እምብርት ሆኖ ሚናውን ሊወጣ ይገባል፡፡

ይህም የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ቀጣይ እድገት ዘላቂነት በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በግሉ ሴክተር በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችም ለአገራዊው ልማት የሚፈለገውን የሰው ኃይል ለማቅረብ ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ብቁ ዜጋ ማፍራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርትና በቴክኒክ ትምህርትና ሙያ ሰልጠና ላይ ውጤታማ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ትምህርቱ ጥራትና ተገቢነት ያለው መሆኑን ከማረጋገጥ አኳያ በፕሮግራሙ ላይ የጎላ ችግር ባይኖርም በሁሉም ተቋሞች በትክክል የሚፈጸም መሆኑን ማረጋገጥና ቀጣይነቱን መገንባት ላይ ልዩነቶች እንዳሉ አመልክተዋል፡፡

የጥራት ተገቢነት ጉዳይ ከትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ጀምሮ በግልጽ በመቀመጡ ሁሉም አካላት ትክክለኛውን አረዳድና ግንዛቤ ይዘው ሚናቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ጥራትን ለማረጋገጥ በሚያስችለው ፕሮግራምና አቅጣጫ ላይ በተግባር እየሰሩ ውጤታማ የሆኑ ተቋማት ቢኖሩም ይህንን የሁሉም ተቋማት ውጤትና ሀብት ለማድረግ በስፋት መስራት እንደሚጠይቅ አብራርተዋል፡፡

በግሉ ሴክተር ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ባለፈው ዓመት በተካሄደ ጥናት የተቋማቱ ደረጃ፣ ጥንካሬና ክፍተት ታይቶ የተወሰደ እርምጃ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

ያንን መሰረት በማድረግም ወደፊት ተጠናክረው እንዲሄዱና የልማት ፕሮግራሙ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ማቅረብ እንዲችሉ ለማድረግ ሚኒስቴሩ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ብለዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ተቋማቱ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ የአንድ ዓመት ተኩል ጉዞ ያሳዩትን ክፍተት አሟልተው ደረጃውን የጠበቀ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ የሚያስችላቸውን ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚካሄደው የምክክር መድረክ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸምና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በሚኒስትሩ ገለጻ የተደረገ ሲሆን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ለአገር እድገት ያለው አስተዋጽኦ፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት አጠባበቅ ስርዓት ተሞክሮዎች ያጋጠሙ ችግሮችና ሊወሰዱ የሚገባቸው የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ኢዜአ ዘግቧል፡፡ (ኢዜአ)