መምሪያው የወተትና የሥጋ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ ነው

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 30 2004 /ዋኢማ/ – በሲዳማ ዞን የእንስሳትን የወተትና የሥጋ ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የእንስሳት ሀብት ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ አብተው ለዋልታ እንዳስታወቁት የወተትና የሥጋ ምርታማነትን የማሳደግ ሥራው እየተካሄደ የሚገኘው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እና የሰው ሰራሽ የማዳቀል ዘዴዎችን በመጠቀም ነው።

የማሻሻያ ፕሮግራሙ የሀገር ውስጥ ዝርያ ያላቸውን  ከብቶች የውጭ ዝርያ ካላቸው ጋር  በማዳቀል አርሶ አደሩን ከዘርፉ ከበፊቱ በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል የሥራ ሂደት አስባባሪው ተናግረዋል፡፡

የማዳቀል ሥራው ከሦስት ዓመት በፊት በሙከራ ደረጃ በሁለት ወረዳዎች መጀመሩን የገለጹት አስተባባሪው በአሁኑ ወቅት ግን በዞኑ 16 ወረዳዎች ለማስፋፋት መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ከ23ሺ በላይ የሀገር ውስጥ ዝርያ ያላቸውን ከብቶች የውጪ ዝርያ ካላቸው ከብቶች ጋር የማዳቀል ሥራ መካሄዱን ገልጸዋል።

የተሻሻሉት ዝርያዎች ሆልስታይንና ጀርሲ የሚባሉ የዝርያ ያላቸው ሲሆኑ የዘር ፍሬውንም  ከደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ተቋም በማስመጣት እየተከናወነ እንደሚገኝም አስተባባሪው ጠቁመው የተሻሻሉት ዝርያዎች ደጋማ የአየር ፀባይ መቋቋም የሚችሉ ከመሆናቸውም በላይ የተሻለ የሥጋና የወተት ምርት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

በተለይ በወተት ምርት መጠናቸው የሀገር ውስጥ ዝርያ ካላቸው ከብቶች በቀን ከ2 እስከ 3 ሊትር ወተት እንደሚገኝ የገለፁት አስተባባሪው ዝርያቸው ከተሻሻሉ ከብቶች ግን በቀን ከ12 እስከ 14 ሊትር ወተት እንደሚገኝ አስረድተዋል።