አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30 2004 /ዋኢማ/ – ኢትዮጵያ በ2025 የተቀመጠውን የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ስትራቴጂው አገሪቱ ከ15 ዓመታት በኋላ የካርቦን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ ያስችላታል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ በተለይ የታዳሽ ኢነርጂን የሃይል ምንጮች በማልማት ፖሊሲውን ውጤታማ የምታደርግባቸውን ተግባራት ከወዲሁ እያካሔደች ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ የገናሌ ዳዋ፣ ጫሞ ጋያዳ፣ የግለገል ግቤ ሶስት እንዲሁም የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራች ሲሆን የታዳሽ ኢነርጂን የማመንጨቱ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
በዚህም አገሪቱ በ2025 የተቀመጠውንና የካርቦን ልቀትን ዜሮ ለማድረስ እንደምትችል አመልክተው የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት በአገር ደረጃ በሁሉም የልማት መስክ በተጠናከረ መንገድ እየተሔደ ነው ብለዋል፡፡
የባዩ ፊዩል፣ የጃትሮፋና ኃይል አመንጪ የሆኑ እጽዋትን የመትከሉ ስራም በስፋት እየተሔደና ውጤት እየተገኘበት መሆኑን አቶ አለማየሁ አስረድተዋል፡፡
የደን ልማት ስራን በተመለከተ በየአመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች እየተተከሉ በመሆኑ ወደ አየር የሚለቀቀው ካርቦን እንዲዋጥ እንደሚያደርግም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረት ደበበ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በየዘርፉ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በታዳሽ የሃይል ምንጭ ከ95 በመቶ በላይ ተጠቃሚ ስትሆን ይህ ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአህጉራዊና በአለም አቀፍ ደረጃ ላለው የሃይል ትስስር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስታውቀዋል፡፡
አገሪቱ ያሏት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በየጊዜው እያደጉ በመሆናቸው ከአካባቢው አገራት ጋር ያላት ግንኙነትም በዚሁ መስክ እያደገ ነው ብለዋል፡፡
በየዘርፉ የምታከናውናቸው ተግባራትም የካርቦን ልቀቱን ከሚቀንሱ ምንጮች እንዲሆን እያደረገች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የካርቦን ልቀትን ከሚያባብሱ ምንጮች አገሪቱን ከማላቀቅ ባሻገር ከኢትዮጵያ ጋር በኢነርጂ የሚተሳሰሩ የአካባቢው አገራት ከታዳሽ ኢነርጂ ዘርፍ ተጠቃሚ አንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
እስከ 2025 ያለው የሃይል ዘርፍ ማስተር ፕላን በታዳሽ ሃይል ላይ የተመሰረቱ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በመሆናቸው የካርቦን ልቀትን ለማስወገድ መፍትሔ እንደሚሆኑ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።