አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 30 2004 /ዋኢማ/ – በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ የሚሳተፉ ባለሃብቶች ቁጥር ከአምስት አመታት ወዲህ እያደገ መምጣቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው የእቅድና መረጃ ስራ አመራር ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሰይድ እንደገለጹት ባለፉት አምስት አመታት በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለመሰማራት ፈቃድ ከወሰዱ ባለሃብቶች መካከል ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡት ወደ ስራ ገብተዋል፡፡
በማምረቻ ኢንዱስትሪ ዘርፍም 6 ሺህ 825 ፕሮጀክቶች ፈቃድ የወሰዱ ሲሆን 220 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል፡፡
ከፕሮጀክቶቹ ውስጥም 814 የሚሆኑት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዘርፉ የሚሳተፉ ባለሃብቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡
ባለሃብቶቹ ከተሳተፉበት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ መካከል የወተት፣ የሰሊጥ፣ የስጋ፣ የጥጥ፣ አትክልትና ፍራፍሬን የማቀነባር ተግባራት እንደሚጠቀሱ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
ዘርፎቹ የአገሪቱን የግብርና ልማት ዘርፍ የሚያሳድጉና በቀጥታ የግብርና ምርቶችን የሚጠቀሙ በመሆናቸው ከመንግስት ማበረታቻ የሚሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከማበረታቻዎቹ መካከልም ከገቢ ግብር ነጻ የሚያደርግ አሰራር መኖሩን ጠቅሰው ይህንን ዘርፍ ማበረታታት ለኢንዱስትሪ ልማት እስትራቴጂው ሰፊ እገዛ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ የሚያስገኘው ገቢ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ 45 በመቶ ድርሻ የሚይዝ ሲሆን መንግስት ዘርፉን ለማሳደግና ከአምስት አመት በኋላ መሪነቱን እንዲረከብ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኤጀንሲው የኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥ ስርአቱን በመቀየር ባለሃብቶች በአንድ ቦታ ብቻ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል አሰራር እየቀየሰ መሆኑን የዘገበው ኢዜአ ነው።