ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ ለብሪቲሹ ዲያጂዮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ተሸጠ

አዲስ አበባ፤ ጥር 02 2004 / ዋኢማ /– ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር በ225 ሚሊዮን ዶላር ለብሪቲሹ ዲያጂዮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ተሸጠ።
የርክክቡን ፊርማ የፈረሙት የፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረመስቀልና የዲያጂዮ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሚስተር ኒክ ብላዝኩዊዝ ናቸው።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ አቶ በየነ ገብረመስቀል እንደገለጹት ዲያጂዮ የጨረታው አሸናፊ በመሆንና የሚፈለግበትን ግዴታ በማሟላቱ ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበርን እንዲረከብ ተደርጓል።

ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር ወደ ግል ይዞታ በመዛወሩ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ተናግረዋል።

የፋብሪካው የማኔጅመንት አባላትና ሠራተኞች ከኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በትብብር በመስራት በአሁን ወቅት ያለውን ምርት ከፍ ማድረግ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

የዲያጂዮ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሚስተር ኒክ ብላዝኩዊዝ በበኩላቸው የፋብሪካው ግዢ መፈጸም በአፍሪካ ባለው የአልኮልና የቢራ ገበያ ውስጥ በሰፊው ለመሳተፍ ያላቸውን ዕቅድ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር ታላቅ ቅርስና ሰፊ ታሪክ ያለው ጠንካራ ብሔራዊ ምልክት እንደሆነም ገልጸዋል።

ለረጅም ጊዜ ከተገነባው ስሙ፣ ከሜታ ገበያና ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ በመሆን እንደሚሰሩም ሚስተር ብላዝኩዊዝ ጠቁመዋል።

ዲያጂዮ የፋብሪካው ባለቤት በመሆኑ በኢትዮጵያ ፈጣን ዕድገት እያሳየ ባለው የቢራ ገበያ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖረው ከማስቻሉም በላይ ቀድሞ ከነበረው የአልኮል መጠጥ ገበያ ጋር የተጣጣመ እንደሚሆንም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የብሪቲሽ አምባሳደር ሚስተር ግሬግ ዶሬይ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት በብሪቲሽ ታዋቂና ግዙፍ ከሆኑት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ዲያጂዮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ የሁለቱን አገራት ግንኙነት የሚያጠናክር ነው።

በተለይ ኢትዮጵያ ባላት ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በመጠቀም ዲያጂዮ ለአገሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ጠቁመዋል።

የሜታን ጥንካሬና ቅርስነት ከዲያጂዮ ዓለም አቀፍ ማንነትና የፈጠራ ሥራ ማረጋገጫዎች ጋር በማዋሀድ ስሙ በገበያ እንዲያድግ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።

ትናንት የተደረገው ስምምነት ግብይቱ ከብሪቲሽ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረግ ተጨባጭ ኢንቨስትመንትን የሚያሳይ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ዶሬይ በተለይ ለአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬት አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ዲያጂዮ ዋተር ኦፍ ላይፍ ፕሮግራምን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋፋት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን በአሁን ወቅት በቀጨኔና በጉዶ አውራጃ አካባቢ ከ60 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የዲያጂዮና ሜታ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ፍራንሲስ አግቦንላሆር በበኩላቸው በገበያ ውስጥ በቀጥታ በመሰማራት፣ የቢራን ገበያ በማነቃቃትና ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችሉ ጥናቶች እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

ዲያጂዮ በዓለም ላይ የአልኮል፣ የቢራና የወይን መጠጦችን በማምረት ግንባር ቀደም የሆነ የብሪትሽ ግዙፍ ኩባንያ ነው።

ከምርቶቹ ውስጥ ጆኒዎከር፣ ክራውን ሮያል፣ ጄ አንድ ቢ፣ ቡካናንስ፣ ዊንድሶር ኤንድ ቡሽሚልስ ዊስኪስ፣ ስሚርኖፍ ሲሮክ ኬተል ዋን ቮድካ፣ ቤሊስ፣ ካፒቴን ሞርጋን፣ ሆዜ ኮርቮ፣ ታንካሪ እና ጊነስ ተጠቃሽ መሆናቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።