በፌደራል ተቋማት የኪራይ ሰብሳቢነትን ለማስቀረት የተጠናከረ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 05 2004 /ዋኢማ/ – በፌደራል ተቋማት የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት ለማስቀረት የተጠናከረ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ መሆኑን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ ገለጹ፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ከ94 የፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ከፍተኛ የሥራ አመራር አባላት ያዘጋጀው ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ድህነትን ለማሸነፍና አስተማማኝ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ለመገንባት አገሪቱ በአሁኑ ወቅት  እያደረገችው ያለው ጥረት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡

በፌደራል ተቋማት የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት ለማስቀረት የተጠናከረ እንቅስቃሴ በመካሄድ ላይ መሆኑን  የጠቆሙት ሚኒስትሩ አሰራርን በየጊዜው መፈተሽ እና አመራሩ በስነ ምግባር የተደገፈ አስተዳደር እንዲከተል ማስቻል ተጠቃሽ  ሥራዎች ናቸው ብለዋል።

መንግስትም የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር የአገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት ጉዞ ለማፋጠን ብርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህ ረገድ የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም በስነምግባር የታነፀ አመራር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

ስነምግባራዊ አመራር ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ ጁነዲን ጠቁመው፣የአመራሮች የስነምግባር መርሆዎች በትክክል ተግባራዊ ካልተደረጉ እየተካሄዱ ባሉት የልማት ስራዎች ላይ ከፍተኛ እንቅፋት በመፍጠር የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚጐዳውም አስገንዝበዋል፡፡

መንግስት በዚህ ዓመት በአጠቃላይ 80 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን አስታውሰው፣ ይህ ከፍተኛ በጀት በአመራሮች አማካኝነት በሁሉም ሕዝባዊ ድርጅቶች ተግባራዊ እንደሚደረግ እና ከአመራሮች ከፍተኛ ስነምግባር እንደሚጠበቅ አመልክተዋል፡፡

በጉባኤው ላይ በስነምግባራዊ አመራር መርሆዎች፣ ስለ ስነምግባራዊ አመራር ተግባራት እና ስነምግባር ያላቸው አመራሮች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመጋፈጥ ሊኖራቸው ስለሚገባ ፈቃደኝነት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ተሰጥቷል።

ስልጠናውን የሰጡት በአሜሪካ የቴይለር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኢግኒ ሃብከር እንደገለጹት አመራር በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ጉዳይ ሆኗል፡፡

የስራ አመራሮች ከሚፈጽሟቸው ስህተቶች መካከል የራስን ጥቅም ማስቀደም፣ ለሕዝብ ፍላጐቶች ግዴለሽ መሆን፣ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት እንደሚገኙበት ዶክተር ኢግኒ  ጠቁመው እነዚህም ደካማ አመራር የሚያስከትሏቸው ችግሮች መሆናቸውን መናገራቸውን የዘገቡት ኢዜአ እና ኤፍ ቢ ሲ ናቸው፡፡