የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከበረ

አዲስ አበባ፤ ጥር 12 2004 /ዋኢማ/ – በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤትክርስቲያን የጥምቀት በዓል ትናንት በድምቀት ተከበረ፡፡
ታቦታቱ ከትናንት በስትያ ከየአጥቢያቸው በመነሳት ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ ወደ ማደሪያቸው ገብተዋል፡፡ ጃንሜዳን ጨምሮ ታቦታቱ በከተማዋ 16 የተለያዩ ቦታዎች አድረው ወደ አጥቢያቸው ተመልሰዋል፡፡

ትናንት ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ወንጌሎች ሲሰበኩ የቆዩ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታውን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤትክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የጥምቀት በዓል ለበርካታ ዐመታት ሳይቋረጥና ሃይማኖታዊ ይዘቱን ሳይለቅ የመጣ ሲሆን ይህንኑ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ምዕመናኑ ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በዓሉ የተሰጠው ለዓለም ሕዘብ ቢሆንም ምሳሌውንና አካሄዱን ይዞ የቆየው በኢትዮጵያ በመሆኑ ሁሉም ጠብቆ ሊያቆየው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በጃንሜዳ ያደሩት ታእካ ነገስት ባእታ ለማርያም፣ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ፣ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዩርጊስ፣ መንበረ መንግስት ቅዱስ ገብርኤል፣ ቀጨኔ ደብረሰላም መድሃኒአለም እና ደብረ ነጉድጓድ ቅዱስ ዩሐንስ ታቦታት ወደ አጥቢያቸው ተመልሰዋል፡፡

ታቦታቱ ወደ የአድባራቱ ሲመለሱ ጥንግ ድርብ የለበሱ ጳጳሳት፣ ካሕናት፣ መነኮሳት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራንና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን ያጀቡዋቸው ሲሆን በርካታ የውጭ አገር ዜጎችም በበዓሉ ላይ  መታደማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡