የዳግም ንግድ ምዝገባ የጊዜ ገደብን ለማራዘም የማሻሻያ አዋጅ ጸደቀ

አዲስ አበባ፤ጥር 25 2004 /ዋኢማ/ – የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዳግም ንግድ ምዝገባ የጊዜ ገደብን ለማራዘም የሚያስችል የማሻሻያ አዋጅ አፀደቀ።

በምክር ቤቱ የጸደቀው የማሻሻያ አዋጅ የዳግም ምዝገባው እስከ ሃምሌ 17 ቀን 2004 ዓ.ም እንዲራዘም የሚያስችል ነው።

የማሻሻያ አዋጁ እንዲጸድቅ የተደረገው ለተደጋጋሚ ተራዝሞ በነበረው የዳግም ንግድ ምዝገባ ጊዜ ያልተጠቀሙ ነጋዴዎች ባቀረቡት ጥያቄ መነሻነት መሆኑም ተገልፆል።

የማሻሻያ አዋጁን የጊዜ ገደብ ማራዘም ነጋዴዎችን ለማበረታታት የተወሰዱ እርምጃዎችን ህጋዊ ለማድረግ እንደሚያስችልም በንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኑረዲን አህመድ ተናግረዋል።

ወደ ህጋዊ መስመር ያልገቡትን ህጋዊ ለማድረግም የዳግም ምዝገባውን ጊዜ ማራዘሙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አቶ ኑረዲን ገለፀዋል።

በሌላም በኩል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ አራት ረቂቅ አዋጆችን ለዝርዝር ዕይታ ወደ ሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

ምክር ቤቱ ለዝርዝር ዕይታ ከመራቸው ረቂቅ አዋጆች መካከል ስደተኞችን በህገ ወጥ መንገድ በየብስ፤ በባህርና በአየር ማስወጣትና ማስገባትን ለመከላከል የወጣውን አለም አቀፍ ፕሮቶኮል ለማጽደቅ የተዘጋጀው ይገኝበታል።

ረቂቅ አዋጁ የተመራው ለውጭ፤ መከላከያና ደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው።

የሴቶችና የህፃናት ዝውውርን ለመከላከል፤ ለመቆጣጠርና የወንጀሉን ፈፃሚዎች ለመቅጣት የቀረበውን አለም አቀፍ ፕሮቶኮል ለማጽደቅ የወጣው ረቂቅ አዋጅ ደግሞ ለማህበራዊ ጉዳዮችና ለሴቶች፤ ወጣቶችና ህፃናት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርቷል።

ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍን ለመቆጣጠር የወጣውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ለማፅደቅ የቀረበው ረቂቅ አዋጅም ለዝርዝር ዕይታ ለህግ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮችና ለውጭ፤ መከላከያና ደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርቷል።

የጦር መሳሪያዎችን፤ መለዋወጫዎችንና አካሎቻቸውን፤ እንዲሁም ፈንጂዎችን በህገ ወጥ መንገድ ማምረትንና ማዘዋወርን ለመከላከል የወጣውን ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮል ለማጽደቅ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅም  ለውጭ፤ መከላከያና ደህንነት ጉዳዮችና ለህግ፤ ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች መመራቱን የዘገበው ኤፍ ቢ ሲ ነው።