በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተደራጅቶ የሽብር ተግባር ለማከናወን በእንቅስቃሴ ላይ የነበረው የአልቃኢዳ ህዋስ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 28 2004 /ዋኢማ/ – የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ የፀረ ሽብር ግብረኃይል በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተደራጅቶ የሽብር ተግባር ለማከናወን በእንቅስቃሴ ላይ የነበረውን የአልቃኢዳ ህዋስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

ግብረኃይሉ ጥር 27/2004 ዓ.ም ለኢሬቴድ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በኢትዮጵያ ላይ የአልቃኢዳ የውጪ ጥቃት ስጋት የነበረና አሁንም ያለ ነው።   በአሁኑ ወቅት የራሷ ዜጎች ከምስራቅ አፍሪካ አልቃኢዳ ጋር ጥብቅ ግንኙነት መስርተው በሀገር ውስጥ በማደረጃት፣ ስልጠናና ትምህርት በመስጠት ሲንቀሳቀሱ የተደረሰባቸው መሆኑን ግብረሀይሉ አስታውቋል።

የተጠርጣሪዎቹ እንቅስቃሴ በሀገሪቱ ከቅርብ አመታት ጀምሮ በመታየት ላይ ያለውን የአክራሪነት ዝንባሌ እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም መሆኑንም ግብረኃይሉ ጨምሮ ገልጿል፡፡

በቁጥጥር ስር የዋሉት ስምንት የሚሆኑት ተጠርጣሪዎች የሽብር ተልዕኳቸውን ለመፈፀም ከሶማሊያ አልሸባብና አልቃኢዳ፣ ከኬኒያ፣ ከሱዳን፣ ከፊሊፒንስ፣ ከሳዑዲአረቢያ እና ደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ የአልቃኢዳ ህዋሳት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መታወቁንም ግብረኃይሉ ገልጿል፡፡

የፀረ ሽብር ግብረኃይሉ የመርማሪ ቡድን በቁጥጥር ስር የዋሉትን ተጠርጣሪዎች በሀገሪቱ የፀረ ሽብር ህግ መሰረት የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ከፍርድ ቤት በመውሰድ ምርመራውን በተጠናከረ ሁኔታ እያከናወነ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡