በዴንማርክ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል 78ሺህ 400 ዶላር ዋጋ ያላቸው ቦንዶች ተሸጡ

አዲስ አበባ፤ ጥር 30 2004/ዋኢማ/ – በዴንማርክ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የዳያስፖራ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት 78 ሺህ 400 ዶላር ዋጋ ያላቸው ቦንዶች ሰሞኑን መሸጡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ሁለት ሺህ የዴንማርክ ክሮነርም በስጦታ ተገኝቷል።

በእንግሊዝ የኢ ፌ ዴ ሪ ኤምባሲና ከስቶክሆልም የኢ ፌ ዴሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በኮፐንሐገን ከተማ በተደረገው ሽያጭ 63ሺህ 400 ዶላር በሽያጭ፣10ሺህ የእንግሊዝ ፓወንድ (ወይም 15ሺህ ዶላር) በቃል መግቢያ ሰነድ ዋጋ ያላቸው ቦንዶች ተሸጠዋል።

በታላቋ ብሪታንያና በስካንዴኒቪያ አገሮች የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ብርሃኑ ከበደና በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ አምባሳደር አብዱልረሺድ ዱለኔ ለፕሮግራሙ ተሳታፊዎች በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ በአማርኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ገለጻ አድርገዋል።

ዲፕሎማቶቹ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በአገሪቱ የተጀመረው የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት እንዲኖረው በሚደረገው እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ቦንድ በመግዛት እንዲሳተፉ አሳስበዋል።

በፕሮግራሙ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካፈላቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤትን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል::